የጋራ ጥረትን የሚሻው የባሕር በር ጥያቄ

You are currently viewing የጋራ ጥረትን የሚሻው የባሕር በር ጥያቄ

ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስጠበቅ ያለ ልዩነት በጋራ መስራት ይገባናል ሲሉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል

በዓለም ላይ ከሚገኙት 195 ሉዓላዊ ሀገራት መካከል 44ቱ የባሕር በር የላቸውም ይላል ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ። ከእነዚህ ውስጥ 31ዱ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው፤ ካዛኪስታን በቆዳ ስፋቷ ትልቅ ሆና ወደብ የሌላት ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ የሕዝብ ብዛት እና ሠፊ ግዛት ይዛ የባሕር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት ተርታ ትመደባለች፡፡

በኢኮኖሚ ልማት እና በድህነት ቅነሳ ዙሪያ በሚያደርጉት ጥናት የሚታወቁት የኢኮኖሚ ባለሙያው ጄፍሪ ሳክስ፣ ከባሕር በር ርቀው የቆዩት እነዚህ ሀገራት እየተጋፈጡት ያለው ችግር ብዙ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ከባሕር ዳርቻ መራቅ ማለት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያዎች ለመድረስ ረጅም እና ውስብስብ የሆነ የየብስ ጉዞ ይጠይቃል፤ ይህ ደግሞ ለወጪ  እና ለገቢ ምርቶች የትራንስፖርት ወጪን በእጅጉ ይጨምራል። በሌላም በኩል ከፍ ባለ የትራንስፖርት ወጪ ሳቢያ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል። በመሆኑም የባሕር በር አለመኖር የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚገታ ትልቅ እንቅፋት ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡

ተጨባጩ እውነት ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለዓመታት የባሕር በርን ጉዳይ ማንሳት እንደነውር አለፍ ሲልም ለእስር የሚዳርግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ቀን ቆጥሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል፤ ሀገራዊ መነጋገሪያም ሆኗል። ጉዳዩ አይነኬ ከመሆን አልፎ አጀንዳ መሆን ችሏል፡፡

ምንም እንኳን አንገብጋቢው የባሕር በር ጉዳይ ለዓመታት ከመወያያ ጠረጴዛው ላይ ርቆ ቢቆይም የኢትዮጵያውያን ህይወት ከባሕር ጋር የተቆራኘ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ እጣንና የዝሆን ጥርስ ጭኖ ለመካከለኛውና ሩቅ ምስራቅ ገበያ የሚያቀርብ ረጅም ተጓዥ ባህርተኛም ነበር፡፡ ልጆቹንም ‘ባሕሩ’ እና ’ባሕሯ‘ ብሎ እየሰየመ ለሺህ ዘመናት ጠረፉን ሲጠብቅና ሲዋደቅ ስለመኖሩም ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይሁንና በክፉ የታሪክ አጋጣሚ በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ከባሕር ርቀው ቆይተዋል የሚሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ናቸው።

በእርግጥ በሴራ ፖለቲካ ምክንያት ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ከባሕር በር እንድትገለል ከተደረገች ጊዜ አንስቶ ሀገር ወዳድ ምሁራን እና የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ መንገድ ጥያቄውን ከማንሳት አልቦዘኑም፡፡ በመንግሥት ደረጃ እንዳይነሳ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ ይከላከል የነበረ የፖለቲካ ስርዓት በመሆኑ የሕዝብ ውይይት ሳይደረግበት ቆይቷል። የባሕር በር የማግኘት ፍላጎትን በግልጽ መሰማት ከተጀመረበት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ጉዳዩ የውጭ ግንኙነት፣ የውስጥ ፖለቲካና የሀገሪቱ የረዥም ጊዜ የልማትና ደኅንነት ስትራቴጂ ጉዳይ ማጠንጠኛ ጭምር እየሆነ መጥቷል።

እዚህ ጋር የሚነሳው ወሳኙ ጉዳይ ታዲያ ኢትዮጵያ ቆርጣ የተነሳችበት ይህ አጀንዳ እውን እንዲሆን የብዙ ባለድርሻ አካላት በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና ሚና ወሳኝ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ምንም እንኳን በውስጣዊ ፖለቲካ እና አስተዳደር ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም አብዛኞቹ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት ህጋዊ እና ኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት ላይ ይስማማሉ። የባሕር በር የሌላት ሀገር በአብዛኛው የውጭ ንግድ እንቅስቃሴዋ በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ ነው። ይህም የትራንስፖርት ወጪን ከማናርም በላይ የፖለቲካ ተጋላጭነትን ይፈጥራል። ስለዚህ ፓርቲዎች፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማጠናከር እና ከውጭ ጥገኝነት ለመላቀቅ የባሕር በር ወሳኝ እንደሆነ ይስማማሉ።

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም የሚሉት ይህንኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ሀሳባቸውን ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት  ክፍል ያጋሩት የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ) ሊቀ መንበር ገብሩ በርሄ ናቸው።

የ‘ኢዴህ’ ሊቀ መንበር ገብሩ በርሄ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በባሕር በር ላይ የመብት ባለቤትነቷን የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት አለባት፡፡ የባሕር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ፓርቲያቸው ይደግፋል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህ ጉዳይ ለሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ከመንግስት ጋር መተባበር አለባቸው፡፡

በአንዳንድ አካላት “አሁን ወቅቱ አይደለም፣ ኢትዮጵያ ልታስቀድመው የሚገባት ጉዳዮች አሏት” ለሚሉና መሰል ጉዳዮች የተሳሳቱ ስለመሆናቸው የሚያነሱት አቶ ገብሩ፣ የባሕር በር ጥያቄን ለማንሳት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ጥያቄው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በአማራ ክልል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢው እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህም በአቶ ገብሩ ሀሳብ ይስማማሉ። ኢትዮጵያ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የባሕር በር አጥታ ስለመቆየቷ የሚገልፁት አቶ ተስፋሁን፣ ጉዳዩ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ አጀንዳውን ማንም ያንሳው የባሕር በር ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲም ኢትዮጵያ ሀብቷን ተነጥቃ ቆይታለች ብሎ እንደሚያምን፣ ፖለቲካም ቢሆን ከሀገርና ብሔራዊ ጥቅም ስለማይበልጥ የባሕር በር ጉዳይን አጥብቀን የምንታገልበት አጀንዳ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

የፖለቲካ ልዩነቶች መኖር ጤነኛና የሚጠበቅ ስለመሆኑ የሚያነሱት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ ልዩነቶቻችን ግን ከሀገር በታች ናቸው ይላሉ፡፡ አያይዘውም ፓርቲዎቹ ጉዳዩን ለዓመታት ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ መሆኑንና አሁንም ቢሆን ለተግባራዊነቱ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን አስጠብቀን ሁላችንም የቆምነው ለህዝብና ለሀገር መሆኑ መረሳት የለበትም ብለዋል፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበትን መንገድ አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በአንድ ህገ ወጥ ቡድን በህገ ወጥ መንገድ የባሕር በሯ ተላልፎ ስለመሰጠቱም ይጠቅሳሉ፡፡ አክለውም ይህ ታሪካዊ ስህተት ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ስለመሆኑና ለነገ የሚባል እንዳልሆነም አንስተዋል፡፡

በአቶ ተስፋሁን አስተያየት የሚስማሙት አቶ ገብሩ፣ “የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ ዓላማችን ስልጣን ይዞ ፖሊሲዎቻችንን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በእንደዚህ አይነት አጀንዳዎች ዙሪያ ግን የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተባብረው ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል፡፡

የባሕር በር ጉዳይ በዋናነት የሚነሳው እንደ ሀገር መውጫ መግቢያ ስላጣን እና ስለታፈንን አይደለም የሚሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ “አሰብን ጠቅሰን የባሕር በር ይገባናል የምንለው አሰብ የኢትዮጵያ አካል ስለሆነ ብቻ ነው።” ይላሉ፡፡ አያይዘውም አላግባብ ከኢትዮጵያ የተወሰደ ስለሆነ፣ ሉዓላዊነትን ያላረጋገጠ የሽግግር መንግስት በተናጥል ውሳኔ አሳልፎ የሰጠው ስለሆነ ነውም ባይ ናቸው፡፡

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ማንሳቷ የወደብ ኪራይ ክፍያ ስለበዛ ወይም የህዝብ ቁጥሯም ስለጨመረ ብቻ ሳይሆን  ተገንጣይና አስገንጣይ ተባብረው በአንድነት የፈጸሙት ታሪካዊ በደል ስለሆነ ነው የአሰብን የኢትዮጵያ አካል አለመሆንን የማንቀበለውና አሰብ ተፈጥሯዊ የኢትዮጵያ የባሕር በርነቱ ዳግም ሊረጋግጥ ይገባል የምንለው ይላሉ። ይህንን ጥያቄ ለማንሳትም ይሁን እንደ ሀገር በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ለመታገልና ጥያቄውን ለማስመለስ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለም ይላሉ፡፡

3D Render of a Topographic Map of Middle East. All source data is in the public domain. Color texture: Made with Natural Earth. http://www.naturalearthdata.com/downloads/10m-raster-data/10m-cross-blend-hypso/ Relief texture: GMTED2010 data courtesy of USGS. URL of source image: https://topotools.cr.usgs.gov/gmted_viewer/viewer.htm Water texture: World Water Body Limits: Humanitarian Information Unit HIU, U.S. Department of State http://geonode.state.gov/layers/geonode%3AWorld_water_body_limits_polygons Boundaries: Humanitarian Information Unit HIU, U.S. Department of State (database: LSIB) http://geonode.state.gov/layers/geonode%3ALSIB_10

ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙም የጠየቁት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን በማጠቃለያ ሀሳባቸው ሊደረጉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡ ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የሚስተዋሉት ጭቅጭቆች መነሻቸው ፖለቲካው ባለመሰልጠኑ የመጡ እንደሆነ የሚያነሱት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ፖለቲካው መሰልጠን እንደሚገባውና ብሔራዊ ጥቅም እና የፓርቲ አጀንዳ ሊቀላቀል አይገባም፣ ችግሮችና የፖለቲካ ልዩነቶች በሀሳብ ሙግት ብቻ ሊፈቱ እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

የባሕር በር ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን በማመን፣ ጉዳዩን ከጠባብ የፖለቲካ ትርፍ አውጥቶ፣ ከምሑራን፣ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሲቪክ ማህበራት እና ከህዝቡ ጋር ሁሉን አቀፍ እና ግልጽ ብሔራዊ ውይይት ማካሄድ። የጉዳዩን ታሪካዊ፣ ህጋዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ገጽታዎች እንዲታወቁ መስራት፡፡ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ዘላቂ የዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲገኝ መጣር እና የባሕር በርን ጉዳይ ለሁሉም የአካባቢው ሀገራት የሚበጅ የጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት አድርጎ ማቅረብ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚጠበቀው ኃላፊነት ስለመሆኑም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይስማማሉ።

በእርግጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ሲያሳዩ የቆዩበት ጥሩ ተሞክሮ አለ። ለዚህም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ዋነኛው ምሳሌ ነው። ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ፓርቲዎች ግድቡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መብት እንደሆነ እና መገንባት እንዳለበት አጥብቀው ደግፈዋል። ይህ በግድቡ ጉዳይ የተፈጠረው የብሔራዊ መግባባት መንፈስ በባሕር በሩ ጥያቄ ዙሪያም ሊደገም የሚገባው ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ከውዝግብ ወጥቶ የሰላማዊና የዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ አሸናፊ እንዲሆን ግፊት ማድረግ በተለይም ፖለቲከኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙሃን በዚህ ጉዳይ ላይ የድርሻቸውን ማበርከት ይኖርባቸዋል የሚለውም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ ነው፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review