ጉባኤው የሚፈጥረው ዕድልና የቤት ስራዎች

You are currently viewing ጉባኤው የሚፈጥረው ዕድልና የቤት ስራዎች

• የኮፕ 32 ጉባኤ በርካታ እንግዶችን ስለሚያሳትፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ምሁራን ገልፀዋል

አዲስ አበባ በዲፕሎማሲ ማዕከልነቷና እያሳየች ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ የዓለምን ዓይንና ቀልብ የሳቡ ትላልቅ ጉባኤዎችን በስፋት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡ በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በብራዚል ቤሌም በተደረገው የኮፕ-30 የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ከሁለት ዓመት በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን የ“ኮፕ-32” የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህን አስመልክቶ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2027 ኮፕ 32ን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ የአፍሪካ ቡድን ተደራዳሪዎች በሙሉ ድምፅ በማፅደቃቸው ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች፡፡ በሰው ልጅ ህልውና ላይ ከተጋረጡ ፈተናዎች አንዱ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የጋራ ጥረት የሚጠይቀውን የኮፕ ጉባኤን እንድንመራ ለተሰጠን እድል እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡

ኮፕ (COP) የሚለው የእንግሊዘኛ ምህፃረ ቃል (Conference of the Parties) የፓርቲዎች ኮንፈረንስ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1992 የፀደቀውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ፈራሚ ሀገራትና በስምምነቱ መሰረት የተደረጉ የኪዮቶና የፓሪስ ስምምነት የአየር ንብረት ለመከላከል የተገቡ ቃል ኪዳኖች ትግበራ የሚገመገምበት፣ተጨማሪ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ድርድርና ውይይት የሚካሄድበት መድረክ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 አስተናጋጅ ሆና መመረጧን ተከትሎ ከሀገር ውስጥ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት አካላት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የኮፕ 32 ዝግጅትን እንዲመሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የኮፕ 32 ተወካይ ፕሬዝዳንት ተደርገው ተመድበዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ቁልፍ የዝግጅት ተግባራትን ለማቀናጀት የሚያስችል የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት ጌዲዮን (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ “ይህ ጉባኤ ከሀገርም ባለፈ አህጉራዊ ፋይዳ ያለው፣ ኢትዮጵያ ዓለምን የምታስተናግድበትና ለቀጣይ ትውልዶች የሚዘልቅ አሻራና ትሩፋት የሚገኝበት ነው” ብለዋል፡፡

“A handbook For Hosting United Nations Climate Change Conference” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመላክተው፣ ጉባኤው በየዓመቱ የሚካሄድ፣ ትልቅና ወሳኝ መንግስታትን የሚያገናኝ መድረክ ነው። በጉባኤው ላይ ከሀገር መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እስከ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የተለያዩ በይነ መንግስታት ድርጅቶች መሪዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የቢዝነስና የትምህርት ማህበረሰብ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ጨምሮ በርካቶች ይሳተፉበታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የኮፕ 32 ጉባኤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም በመሆኑ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ችግሮች ተጠቂና ተጋላጭ ብቻ ሳትሆን መፍትሔ አፍላቂና አመራር የምትሰጥ እንድትሆን መስራት ይጠበቃል፡፡    

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ 32)ን እንድታስተናግድ መመረጧ ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ታሪካዊ ነው፡፡ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ያሳያል። ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት  የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን በስኬት በማስተናገድ እምቅ እና ጠንካራ ተቋማዊ አቅም እና ልምድ አላት። የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ እና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ ጉባኤውን እንድታስተናግድ መመረጧ በዓለም አቀፍ ትብብር ያላትን ማዕከላዊ ሚና የበለጠ እንደሚያሳድግ ያነሱት ሊቀ መንበሩ፣ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት (UNFCCC) እና አጋሮች ጋር በመሆን ኮፕ 32 ሁሉን አካታችና ውጤታማ በማድረግ የአፍሪካን የአየር ንብረት የቅድሚያ ትኩረቶች የበለጠ ለማራመድና ዓለም አቀፍ አጋርነት ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ትላልቅ ዓለም ዓቀፍ ኹነቶችን ማስተናገድ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን በሰፊው ገንብታለች፡፡ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ በኮሪደር ልማትና ወንዝ ዳርቻ ልማት መንገዶችን የማስፋት፣ ደረጃቸውን የማሳደግ፣ የእግረኛና ሳይክል መንገዶችን የመገንባት፣ አረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋት ፅዱና ውብ ማድረግ ችላለች፡፡

ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግስታት በአስተዳደር፣ ድህነትና ዘላቂ ልማት ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የፖለሲ አማካሪ፣ በአፍሪካ ሰብዓዊ ኔትዎርክና የተለያዩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢና አባል በመሆን ሰርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚሰሩበት ወቅት እንዲሁም በቅርቡ በተካሄዱት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ዱባይ እና በቅርቡ ብራዚል በተካሄዱ የኮፕ ጉባኤዎች ላይም ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ ተሳትፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኮፕ 32 ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡

ጉባኤውን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ የተመረጠችው አንደኛው ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ አጀንዳን ቀዳሚ አድርጋ በመስራቷ ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በአረንጓዴ አሻራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ በመትከል የተገኘው ውጤት ነው። ከዚህ ባሻገር አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብሎም ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን የምትወክል ከተማ በመሆኗ እድሉን እንድታገኝ አድርጓታል ብለዋል፡፡

በቅርቡ በብራዚልም ቤሌም በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከ50 ሺህ በላይ እንግዶች ታድመዋል፡፡ ብራዚል በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ በመገንባት ጉባኤውን ማካሄድ ችላለች። ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን ጉባኤ ለማስተናገድም ኢትዮጵያ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባታል። በአንድ ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት እንደመሆኑ፣ ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከትራንስፖርት ጀምሮ የመንገድ፣ የሆቴል፣ አዳራሽና ሌሎች አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ያስገነዝባሉ፡፡

በጉባኤው በርካታ እንግዶች የሚሳተፉበት በመሆኑ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ በአንዳንድ አካላት የሚናፈሰውን “ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም፤ ከከተማ እንዳትወጡ” የሚለውን ትርክት ይቀይራል፡፡ ይህም ቱሪስቶች በስፋት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ይስባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን አመኔታ በማሳደግ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ያበረታታል ይላሉ፤ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፡፡

ኢትዮጵያ ለጉባኤው ተሳታፊዎች የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የምታደርገው ዝግጅት የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ዝግጁነትን በማሳደግ በኩልም ጥቅም ያስገኛል። በቀጣይ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋሙበትና ጥናትና ምርምር የሚደረግበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

የምጣኔ ሀብት ምሀሩ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መከሰት የጎላ ዓይነት አስተዋፅኦ ሳይኖራት የችግሩ ተጠቂና ሰለባ  ናት፡፡ ከዚህ አኳያ አፍሪካን ራሷን በመቻል ከችግሩ እንዴት መውጣት ትችላለች? የሚለውን አጀንዳ ኢትዮጵያ መምራት የምትችልበትን እድል ይፈጠራል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ይንገስ ዓለም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኮፕ 32 ጉባኤ ትልቅና በርካታ ሰዎች የሚታደሙበት በመሆኑ በብዙ መልኩ ትርፋማ ያደርጋል፡፡ የአዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ከፍ ያደርጋል፡፡ ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማሳየትና ለመሸጥ ያስችላል፡፡ የኢትዮጵያ ተወካዮችና ተሳታፊዎች ከተለያዩ ሀገራት ተሳታፊዎች ጋር የሚገናኙበት፣ የሚነጋገሩበትና በዚያውም ሀገርን ማሳወቅ የሚቻልበትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚጠናከርበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለእንግዶች ከትራንስፖርት አንስቶ የምግብና መኝታ አገልግሎቶች በሚቀርብበት ወቅት የሚገኘው ገቢ ለከተማና ሀገር ትልቅ ትርጉም አለው። እንግዶቹ ባገኙት አገልግሎት የሚረኩ ከሆነ የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም በከተማዋ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን የሚጎበኙበት ሁኔታ ይፈጠራል” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከኡራኤል እስከ ብራስ፣ ከቦሌ መድኃኔዓለም- ጎላጎል እስከ እንግሊዝ ኤምባሲ የሚዘልቀውን የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እና የፒኮክ (ማዕከላዊ) ፓርክ ግንባታን እንቅስቃሴ በመስክ በመገኘት በጎበኙበት ወቅት፣ “ኢትዮጵያ የዓለምን ትኩረት የሚስበውን የኮፕ 32 ጉባኤን የምታስተናግድ መሆኗ እድለኛ ናት” ብለዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ የሚከናወንበት አካባቢ አንዱ ጉባኤው የሚካሄድበት ማዕከል በመሆኑ አስቀድመዉ የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “የኮፕ 32 ጉባኤ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት በመሆኑ፣ ጉባኤው በአዲስ አበባ መዘጋጀቱ ከሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ በተጨማሪ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ትስስር እንዲሁም መሰል ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ወደ ሀገራችን በቀጣይነት ለማምጣት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

“መላው የከተማችን ነዋሪዎችና የንግዱ ማኅበረሰብ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ጉባኤው ይዞት የሚመጣውን መልካም ዕድል አሟጥጠን እንድንጠቀም እና ለጉባኤው ስኬታማነትም ከወዲሁ ሁላችንም ዝግጅት እናድርግ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ታዳሚዎች የሚሳተፉባቸውን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በማስተናገድ ጥሩ ልምድ አላት የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ይንገስ (ዶ/ር)፣ “የኮፕ 32 ጉባኤ የተሳካ እንዲሆን መንግስትና ማህበረሰቡ በተናበበና በተቀናጀ መልኩ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆቴሎችና የተለያዩ አገልግሎት ሰጪዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የመብራት፣ ውሃ፣ ኢንተርኔት፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች አገልግሎቶችን የተቀላጠፈ በማድረግ፣ እንግዳ ተቀባይነታች በተግባር ማሳየታችንን አጠናክረን ማስቀጠል ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review