በከተማዋ በ227 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ግብይት እንዲፈጸም እየተደረገ ነው
15 ምርት አቅራቢ ነጋዴዎች ላይ የፅሑፍ 6ቱ ላይ ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ እንዲሁም 5ቱ ላይ ትስስራቸውን በማቋረጥ በተመደቡበት ቦታ ምርት እንዳያቀርቡ ተደርጓል
አዲስ አበባ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት ከተማ ትሆን ዘንድ ከተማ አስተዳደሩ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከዚህ ውስጥ ለኑሮ ውድነቱ መፍትሔ ይሆኑ ዘንድ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉትን የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም በእነዚህ ገበያዎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ከማድረግ ባሻገር በተጨባጭ የኑሮ ውድነቱን ከማቃለል አንፃር እያበረከቱት ስላለው አስተዋጽኦ ከሸማቹ ማህበረሰብ፣ ከሻጮች እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ያሰባሰባቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አጠናቅሯቸዋል፡፡
ሸማቾች ስለግብይቱ ያላቸው አስተያየት
ወይዘሮ ሲፈን ሙሉነህ ይባላሉ፡፡ ነዋሪነታቸው አዲስ ሰፈር አስኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን የቅዳሜና የእሁድ ገበያ ላይ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ሲሸምቱ አግኝተናቸዋል፡፡ በሳምንት አንዱን ቀን ማለትም ቅዳሜን ለአስቤዛ መሸመቻ በሚል አቅደዋል፡፡ በተለይ ትኩስ የግብርና ምርቶችን እንደ ሽንኩርት፣ ድንች እንዲሁም ቲማቲም ያሉ ምርቶችን ይገዛሉ፡፡ በእነዚህ ገበያዎች በመደበኛ ሱቆች ላይ ከሚሸጠው ቢያንስ የ15 ብር ልዩነት እንዳለው የሚናገሩት እኚህ እናት፣ የተረፋቸውን ብር አብቃቅተው ለሌላ ነገር መግዣ ጭምር እንደሚሆናቸው ገልፀዋል፡፡
በእነዚህ ገበያዎች አልፎ አልፎ የሚያስተውሏቸው እንከኖች ባይጠፉም፤ እርሳቸው ግን የተለጠፈውን የሰንበት ገበያ ዋጋን መሰረት ያደረገ ግብይት እንደሚከውኑ ተናግረዋል፡፡ ይህ መረጃ በተጠናቀረበት ወቅት አንደኛው ድንኳን የተለጠፈው ዝርዝር ላይ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 35 ብር እንደሆነ ቢጠቀስም፣ ሻጭው አካል 45 ብር የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጊዜ በተቀመጠው ዋጋ መሰረት እንዲሸጥ ካልሆነ ግን ቅሬታ እንደሚያቀርቡ ሲናገሩ ወዲያው ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ ግብይት መፈጸም ችለዋል፡፡ በተመሳሳይም የአንድ ኪሎ ቲማቲም እና ድንች ዋጋ በቅደም ተከተል በ40 ብር እና በ25 ብር እንደሸመቱ ተናግረዋል፡፡

አቶ ታሪኩ አርጋው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ንግድ ጽህፈት ቤት ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ላይ ለሚደረገው ግብይት ከምርት ጥራት እንዲሁም ከዋጋ ጭማሪ ጋር በተገናኘ ለሚነሱ ቅሬታዎች በቅርበት ሆነው ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በተለይም ለቀረቡ የምርት አይነቶች የተቀመጠውን የዋጋ ዝርዝር ታሳቢ በማድረግ ግብይት በማይፈፅሙ ሻጮች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶችን በጥራት ብሎም በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ነጋዴዎች የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ ይገባሉ፡፡ ከዚህ የስምምነት ሰነድ ውጭ ሲነግዱ በተገኙ አካላት ላይ የቃል፣ የፅሑፍ እንዲሁም ከትስስር እንዲወጡ እስከማገድ የደረሰ ስራ ይሰራል፡፡ ከሀምሌ ወር 2017 ዓ.ም እስከ ህዳር ወር 2018 ዓ.ም ድረስ ቁጥራቸው 6 ለሚሆኑ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ነጋዴዎች ላይ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ስለመሰጠቱ አስታውቀዋል፡፡
ሌላኛውን ቅኝት ያደረግነው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ጨርቆስ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የቅዳሜና እሁድ ገበያ ላይ ነው። እለቱ እሁድ በመሆኑ በርካታ ሰዎች አስቤዛ ሲሸምቱ ተመልክተናል፡፡ ከእነዚህ መካከል ወይዘሮ ትዝታ ምትኩ አንዷ ናቸው፡፡ ከግብርና ምርቶች ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርት የሆነውን አንደኛ ደረጃ የዳቦ ዱቄት እና ፓስታ ለመሸመት መጥተዋል፡፡ ከዋጋ አንፃር እንደ ቅደም ተከተላቸው አንዱን ኪሎ በ40 ብር፣ በ25 ብር፣ በ115 ብር እና በ92 ብር ሸምተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ትዝታ ገለፃ፤ በእነዚህ ገበያዎች ያለው ዋጋ በመደበኛ ሱቆች ካለው ጋር ሲነጻጸር በትንሹ የ15 ብር ልዩነት አለው፡፡ በርከት ያሉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአንድ ቦታ ላይ ማግኘት ችለዋል፡፡
ከግብይት ሂደቱ ጋር በተያያዘ ትዝብታቸውን፣ “አንዳንድ ነጋዴዎች እንደ ቲማቲም ድንች ያሉትን ምርቶች ከተበላሸው ጋር ቀላቅለው ይሸጣሉ” ሲሉ አጋርተዋል፡፡
አቶ አዲሱ በየነ በአስተያየታቸው፣ “እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ ጥቅል ጎመን፣ ፎሶሊያ፣ ነጭ ሽንኩርት እና መሰል ምርቶችን እሸጣለሁ። ደንበኞቻችን በምንሰጣቸው አገልግሎት ተደስተው ቀጣይም እንዲመጡና የእኛን ምርት እንዲገዙ እንፈልጋለን፡፡ ያንን ለማድረግ ደግሞ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማቅረብ እንዲሁም መንግስት እንድንሸጥ ባወጣልን ተመን መሰረት ግብይት መፈፀም ይጠበቅብናል” ብለዋል፡፡
ክፍተቶችን ለመሙላት የተሄደበት ርቀት
በመዲናዋ ፍትሐዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ከማድረግ አኳያ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እና ጥራት ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ ስለመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የንግድ ግብይት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ መከተ አዳፍሬ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። “የከተማዋን ነዋሪ የኑሮ ውድነት ጫና መቀነስ ያስችል ዘንድ እነዚህ ገበያዎች ሁነኛ መፍትሔ ናቸው። እንደ ከተማ ባሉን አስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ቁጥራቸው 227 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎችን በመክፈት ትርጉም ያለው ስራ እየሠራ ይገኛል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ መከተ ገለፃ፤ ባሳለፍነው 2017 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 219 የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ነበሩ፡፡ በያዝነው 2018 በጀት ዓመት ቁጥራቸውን ወደ 240 ለማድረስ ቢሮው አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በአንድ ወረዳ ከአንድ በላይ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ እንዲኖር በማድረግ የተደራሽነት አድማሱን የማስፋት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ሲመሰረት የራሱ የሆነ የአሰራር ሂደት አለው የሚሉን አቶ መከተ ከአሰራሮቹ አንዱ ምርቶችን የሚያቀርቡ አካላት በሙሉ ከንግድ ተቋም ጋር የውል ስምምነት ይገባሉ። መንግስት በሚተምነው ዋጋ ለመሸጥ ፈቃደኛ የመሆን፣ ምርቶችን በጥራትና ደህንነቱ በተጠበቀ አኳኋን የህብረተሰቡን ጤና በማይጎዳ መልኩ ማቅረብ፣ ሸማቹ ህብረተሰብ ለሚከፍለው ዋጋ ተመጣጣኝ የሆነ ምርት የመስጠት (ሚዛን አለመቀሸብ) የሚሉና ሌሎች በርካታ ህጎችን ያካተተ የውል ስምምነት እንደሚፈጽሙ አስረድተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፣ “የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በየሳምንቱ አርብ አርብ አጠቃላይ የከተማዋን የንግድ ሁኔታ በመመልከትና የዋጋ ጥናት በማድረግ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ መሸጫ ዋጋ ተመን ያወጣል፡፡ የወጣው ተመን ለሁሉም ወረዳዎች ባለን የማህበራዊ ሚድያ ግንኙነት አማካኝነት እንዲደርሳቸው ተደርጎ በእያንዳንዱ አቅራቢ ድንኳን ላይ ዋጋው እንዲለጠፍ ይደረጋል፡፡ በተለጠፈው ዋጋ መሸጥ የአቅራቢው ግዴታ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ችግር የሆነውን ነገር ሲገልጹም፣ “መንግስት ዋጋ ተምኖ ይለጥፋል፡፡ ነገር ግን ሸማቹ ማህበረሰብ ዋጋ ስንት ነው? ብሎ የመጠየቅ አዝማሚያ በስፋት አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሻጩ ዋጋ ጨምሮ እንዲናገር እድል ይፈጥራል። መንግስት ህግን ለማስከበር በሚሰራው ልክ ማህበረሰቡም ማገዝ አለበት፡፡ ዋጋ ከመጠየቅ ይልቅ የተፃፈውን አይቶ መክፈል ቢችል የተሻለ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
እንደ የንግድ የግብይት ማስፋፊያ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር የተጠናከረ የስራ ክንውን እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ባለሙያዎችም በተጠናከረ አግባብ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ፣ ህገ ወጥነትም እንዳይፈፀም እየተሰራ ይገኛል፡፡ ህግ ተላልፈው በተገኙ የምርት አቅራቢዎች ላይ ደረጃ በደረጃ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፡፡ እንደ ጥፋቱ ሁኔታ የቃል ማስጠንቀቂያ፣ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ከትስሰር እንዲወጡ በማድረግ በተመደቡበት ቦታ ምርት እንዳያቀርቡ የሚደረግበት አግባብ አለ፡፡
ከእርምጃ በፊት ህብረተሰቡም፣ ምርት አቅራቢውም ስለተቀመጡ ህጎች ጠንቅቆ እንዲያውቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመጠቀም ተገቢውን እውቀት እንዲያገኙ የማስቻል ስራ መሰራቱንም አክለዋል፡፡
በያዝነው 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ውስጥ ወደ 26 የሚደርሱ በተለያዩ ጥፋቶች ላይ የተገኙ አቅራቢዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ሚዛን የቀሸቡ፣ ከተለጠፈው የዋጋ ዝርዝር ውጪ ሲሸጡ የተገኙ፣ የምርት ጥራት ጉድለት ያለባቸውን አካላት እንደየ እርከኑ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተሰርቷል። በዚህም መሰረት 15 ምርት አቅራቢ ነጋዴዎች ላይ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 6ቱ ላይ የቃል ማስጠንቀቂያ እንዲሁም 5ቱ ላይ ከትስሰር እንዲወጡ በማድረግ በተመደቡበት ቦታ ምርት እንዳያቀርቡ የተደረገበትን አግባብ አስረድተዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን