በልኩ ያልተጠቀምንበት ሀብት

You are currently viewing በልኩ ያልተጠቀምንበት ሀብት

በመዲናዋ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ 60 በመቶው ለኮምፖስት መዋል የሚችል መሆኑ ተጠቁሟል

እንደከተማ ለኮምፖስት መዋል ከሚችለው ቆሻሻ ውስጥ ወደ 0 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ብቻ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሚገኝ ተመላክቷል

ወጣት ብሩክ ፀሐይ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ እያለ ነበር ወደፊት የሚሰማራበትን ስራ ማለም የጀመረው፡፡ በባዮቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ ሲማር ቆሻሻን በማከም መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል የተረዳውን ሀሳብ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በማምጣት ወደ ተግባር ለመቀየር ተነሳ። ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቅም በሚሰማራበት ስራ ዙሪያ መጠየቅ ሀሳብ (ፕሮፖዛል) አዘጋጅቶ ነበር የወጣው፡፡

ወጣት ብሩክ በ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ህልሙን እውን ለማድረግ በሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በመግባት በከተማ ግብርና ዘርፍ ስልጠና ወስዷል፡፡ በዚያ አጋጣሚም ተደራጅተው አብረውት የሚሰሩ ጓደኞችን አገኘ፡፡ በ2013 ዓ.ም አስር አባላትን በማቀፍ ደረቅ ቆሻሻን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ለማምረት ተደራጅተው ወደ ስራ እንደገቡ አብራርቷል፡፡

የብሩክ፣ ሰላማዊትና ጓደኞቻቸው ኮምፖስት ማምረት ሽርክና ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ወጣት ብሩክ እንደሚናገረው፣ ማዳበሪያ ለሀገራችን ኢኮኖሚ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማምረት ራሳቸውን ለመለወጥና ለሀገር እድገትም የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት በኮምፖስት ዘርፍ ተሰማርተዋል። ስራውን ሲጀምሩም ከስኬት ባንክ (የቀድሞ አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም) 30 ሺህ ብር ብድር ወስደዋል፤ ከሚኖሩበት ከየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አስተዳደር የስራና ክህሎት ጽህፈት ቤት 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመስሪያ ቦታ አግኝተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ስራው አዲስ ከመሆኑ አኳያ ወደ ገበያ ለመግባት የተለያዩ ፈተናዎችን ማለፍ ግድ ብሏቸዋል፡፡ የማህበሩ አባል እና ኦዲተር ወጣት በቀለ ረጋና እንደሚናገረው፣ ስራውን ከጀመሩ በኋላ ለወራት ያለምንም ደመወዝና ገቢ ግብአት ለማሰባሰብ በእግራቸው ረጅም ርቀት ይጓዙ ነበር፡፡ ሆኖም ነገን ተስፋ በማድረግ ጠንክረው በመስራታቸው ምርቱን በጥራትና በስፋት በማምረት ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡

እነብሩክ ኮምፖስት (የተፈጥሮ ማዳበሪያ) ለማምረት የተለያዩ ሂደቶችን ይከተላሉ፡፡ ግብአት ከመሰብሰብ ጀምሮ የተሰበሰበውን የመቀላቀል፣ ወደ ሼድ በማስገባት አየር እንዲያገኝ የማድረግ እንዲሁም ጠፈፍ ያለውን በወንፊት በማጥራት ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ብሩክ እንደገለፀው፣ ለኮምፖስት ምርት የሚሆነውን ግብአት በዋናነት የሚያገኙት ከገበያ ማዕከላት ነው፡፡ የካራ የቁም እንስሳት የገበያ ማዕከል፣ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት፣ የአትክልት የገበያ ማዕከሎች፣ ጭማቂ ቤቶች፣ የከብትና ዶሮ እርባታ ላይ ከተሰማሩ በግዥና በነፃ ያገኛሉ፡፡ የምግብ ተረፈ ምርቶች፣ የሙዝ ልጣጭ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ሰጋቱራና የተለያዩ መበስበስ የሚችሉ ምርቶች ለኮምፖስት ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡

“ቆሻሻ ቆሻሻ እንጂ የሀብት ምንጭ ተደርጎ አይወሰድም ነበር” የሚለው የማህበሩ አባል ወጣት በቀለ፣ ዘርፉ ትልቅ አቅምና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመረዳት የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው ምርታቸውን በስፋት እያቀረቡ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡ አንድ ኪሎ ኮምፖስት ለተጠቃሚዎች በ4 ብር ሲያቀርቡ መንግስት የሶስት ብር ድጎማ በማድረግ 7 ብር ያገኛሉ፡፡ በኩንታል ደግሞ 700 ብር ያቀርባሉ፡፡  በአሁኑ ወቅት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 400 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) የማምረት አቅም ላይ ደርሰዋል፡፡

የምርቱ ተጠቃሚዎችም በዋናነት በአረንጓዴ ልማት፣ ችግኝ በማፍላት፣ የመንገድ አካፋዮችን ዕፅዋት በመንከባከብ የሚሰሩ ማህበራት፣ መኖሪያ ቤቶች፣ ፓርኮች እንዲሁም የግል ተቋማት ናቸው፡፡ ከእነብሩክ ኮምፖስት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል በመንገድ አካፋይ የተተከሉ ዕፅዋትን በመንከባከብ እየተሳተፉ የሚገኙት ጀማል፣ ፀሐይነሽና ጓደኞቻቸው የአረንጓዴ ልማት ማህበር አንዱ ነው፡፡

የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጀማል በየነ እንደሚናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 የሚገኝ 4 ሺህ 800 ስኩዌር ካሬ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ላይ የሚገኙ ዕፅዋትን እየተንከባከቡ የሚገኙ ሲሆን፤ ለዕፅዋት የሚያስፈልገውን ማዳበሪያም እነብሩክ ከሚያዘጋጁት ማዳበሪያ በዓመት አራት ጊዜ እየገዙ ይጠቀማሉ፡፡ በአንድ ጊዜ 72 ኩንታል ማዳበሪያ የሚገዙ ሲሆን ማዳበሪያው ዕፅዋት ፋፍተው እንዲያድጉ እያስቻለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት የብሩክ፣ ሰላማዊትና ጓደኞቻቸው ኮምፖስት ማምረት ሽርክና ማህበር ካፒታል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በተጨማሪም የራሱ የሆነ መስሪያ ቦታና መፍጫ ማሽኖች አሉት። የማህበሩ አባላት ከራሳቸው ባለፈ ለአራት ወገኖች በቋሚነት እና ለአምስቱ ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ብሩክ ተናግሯል፡፡

አዲስ አበባ በ2013 ዓ.ም የበካይ ጋዝን በሚያስቀር ዘመናዊ ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በመዘርጋት በC40 የከንቲባዎች ፎረም ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ አሸናፊ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከተማዋን ለእውቅና ያበቃትም ለበካይነት የተጋለጠ የነበረውን የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት በማስቀረት ደረቅ ቆሻሻ በመልሶ መጠቀም ለአረንጓዴ ልማትና የጓሮ አትክልት ልማት ስራ የሚውልበትን ስርዓት በመዘርጋቷ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ደረቅ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀምና ለኮምፖስት በማዋል የተሻለ እንቅስቃሴ እያሳየ ያለውን የእነብሩክ ማህበር የስራ እንቅስቃሴ በአካል መጥተው እንደጎበኙና እንዳበረታቷቸውም ወጣት በቀለ ያነሳል።

እነብሩክ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አላቸው፡፡ በረጅም ጊዜ ደግሞ በአፍሪካ ትልቁ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ የመሆን ርዕይም አላቸው፡፡

ደረቅ ቆሻሻን በስፋት ወደ ሀብት ወይም ኮምፖስት ምርት ለመቀየር የመንግስትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ወጣት ብሩክ ያነሳል፡፡ የፋይናንስ፣ የማምረቻ ቦታ፣ ማሽን ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ስራው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን፣ የተማረ የሰው ሀይል በዘርፉ እንዲሰማራ፣ የገበያ ትስስሩም ከከተማ ባሻገር ገጠር ድረስ አርሶ አደሮች ላይ መድረስ የሚችልበት ዕድል እንዲፈጠር ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን በማምጣት፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ማሽኖችን በመፈብረክ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግስት አሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ የበለጠ ቢያጠናክር ዘርፉ ውጤታማ መሆን ይችላል፡፡

እንደ ከተማ ምን እየተሰራ ነው?

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የመልሶ መጠቀምና ዑደት ማድረግ ቡድን መሪ አቶ በላይ አለማየሁ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ስራዎች መካከል ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብት መቀየር አንዱ ነው። በዚህ ረገድም ቁርጥራጭ ብረታ ብረት፣ ወረቀት፣ ካርቶን፣ የውሃ መያዥያ ፕላስቲኮችና የመሳሰሉ የቆሻሻ ዓይነቶች ለመልሶ መጠቀም እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህም በከተማዋ ከሚመነጨው ቆሻሻ 18 በመቶ አካባቢ ድርሻ አላቸው። 60 በመቶ የሚሆነው ደረቅ ቆሻሻ የሚበሰብስና ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርት (ኮምፖስት) መዋል የሚችል ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ አደገኛና ልዩ ልዩ ቆሻሻዎች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ሰው በነፍስ ወከፍ በቀን 0 ነጥብ 45 ኪሎ ግራም ቆሻሻ ያመነጫል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በከተማ ደረጃም በቀን ከ3 ሺህ ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ እንደሚመነጭ ይገመታል፡፡ የሚበሰብስ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት በመቀየር ስራ ላይ 55 ማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደከተማ ለኮምፖስት መዋል ከሚችለው ቆሻሻ ውስጥ ወደ ዜሮ ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ከደረቅ ቆሻሻ 5 ሺህ ቶን ኮምፖስት በማህበራት አማካይነት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ተይዞ፤ 5 ሺህ 460 ቶን በማምረት ማቅረብ ተችሏል፡፡ ከተመረተው ኮምፖስት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከ38 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝተዋል፡፡ 

በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት ከሚበሰብስ ደረቅ ቆሻሻ 7 ሺህ ቶን ኮምፖስት ለማምረት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዘንድሮ ሩብ ዓመትም 1 ሺህ 750 ቶን ኮምፖስት ለማምረት ታቅዶ 1 ሺህ 67 ቶን ኮምፖስት በማምረት ከ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ከእቅድ አኳያ አፈፃፀሙ 65 በመቶ ሲሆን፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት ሼድ የሌላቸውና የክረምት ወቅትም ስለሆነ ብዙ ምርት ባለማምረታቸው እንዲሁም የተጠቃሚው ፍላጎት አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ በበጋ ወራት ማህበራቱ የሚያመርቱት ምርት እየጨመረ ይሄዳል። ለምሳሌ በጥቅምት ወር 583 ቶን ለማምረት ታቅዶ 612 ቶን በማምረት ከእቅድ በላይ ማከናወን ተችሏል፡፡

አቶ በላይ እንደሚገልጹት፤ በከተማዋ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የሚበሰብስ እና ወደ ኮምፖስት መቀየር የሚችል ነው፡፡ ይህ ቀላል ቁጥር አይደለም፡፡ አቅም ኖሮ በሙሉ ወደ ኮምፖስት መቀየር ቢቻል በዘንድሮ ዓመት ይመነጫል ተብሎ ከታቀደው (856 ሺህ 135) ደረቅ ቆሻሻ ወደ 513 ሺህ 681 ቶን ኮምፖስት ማምረት ይቻላል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ያስችላል ማለት ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የሚበሰብስ ቆሻሻ ወደ ቆሻሻ መጣያ ቦታ (ላንድፊል) በማጓጓዝ እየተወገደ ይገኛል፡፡ ቆሻሻን ወደ ሀብት መቀየር ላይ በሰፊው ቢሰራ ወደ ላንድፊል የሚሄደውን መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ፣ ብክለትን መከላከል፣ ለበርካቶች የስራ ዕድል መፍጠርና ገቢ ማስገኘት ይቻላል፡፡ በዘንድሮው ዓመት መበስበስ ከሚችለው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ አንድ በመቶ የሚሆነውን ወደ ኮምፖስት ለመቀየር ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

አቶ በላይ እንደሚገልፁት፣ ከደረቅ ቆሻሻ ኮምፖስት ማምረትን በስፋት ከመተግበር አኳያ የተለያዩ ፈተናዎች አሉ፡፡ አንደኛ ኮምፖስት ማምረት ረጅም ጊዜ የሚፈልግ መሆኑ ነው፡፡ የመጨረሻውን ምርት ለማግኘት ቢያንስ የሁለት ወር ጊዜ ይወስዳል፡፡ ሌሎች ለመልሶ መጠቀም የሚውሉ ቆሻሻዎች ግን ወዲያው ተሰብስበው በቶሎ ገቢ ማግኘት ያስችላሉ፡፡ ሁለተኛ የኮምፖስት ዝግጅትና ማምረት ሰፊ የመስሪያ ቦታ ይፈልጋል፡፡ ስራውን ለማከናወን የራሱ የሆነ እንደ አልባሳት፣ አካፋና የተለያዩ የስራ መሳሪያዎች ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ኮምፖስቱን በዋናነት የሚጠቀሙት በከተማዋ በአረንጓዴ ልማትና እንክብካቤ የተሰማሩ አካላት ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብት የመቀየር ስራ በተለይ ኮምፖስት ማምረት የተጀመረው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ነው። በወቅቱም ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ውስጥ በመልሶ መጠቀምና ኮምፖስት እየዋለ የነበረው 6 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በ2013 ዓ.ም በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራት 1 ሺህ 560 ቶን ኮምፖስት በማምረት ለገበያ አቅርበዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም 5 ሺህ 460 ኮምፖስት ማምረት ተችሏል፡፡ ይህም በየጊዜው የኮምፖስት ምርት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን እንደሚያሳይ አቶ በላይ ያስረዳሉ፡፡

የኮምፖስት ምርትን ለማሳደግ በማዕከል ደረጃ ኮምፖስት የሚመረትባቸው ማዕከላት ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ አንደኛው የመልሶ መጠቀምና ኮምፖስት የሚመረትበት ማዕከል ግንባታ በቦሌ አራብሳ አካባቢ እየተከናወነ ሲሆን፤ ይህም ደረቅ ቆሻሻን በመለየት ለመልሶ መጠቀምና ኮምፖስት በስፋት የሚውልበትን ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡

ሌላው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያለውን የግብርና ምርቶችና የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን ለመጠቀም የኮምፖስት ማዕከል ለመገንባት የቦታ ልየታ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 እንዲሁ ሼድ በመገንባትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ኮምፖስት በስፋት ለማምረት እቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ከዚህም ባሻገር በተያዘው በጀት ዓመት በከተማዋ በሁሉም (በ119) ወረዳዎች አንድ አንድ በኮምፖስት ማምረት የተሰማሩ ማህበራትን ለማቋቋም ጊዜያዊ የቦታ ልየታ ስራ ተጀምሯል፡፡ ይህም በዘርፉ የሚሰማሩ ማህበራት ቁጥርና የሚመረተውን ኮምፖስት መጠን በእጥፍ ማሳደግ የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከስራ እና ክህሎት ቢሮ፣ ከመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ በላይ ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በኮምፖስት ማምረት ለተሰማሩ ማህበራት የክህሎት ድጋፍ፣ የስራ መሳሪያዎች (አካፋ፣ አልባሳት፣ ቴርሞሜትርና የተለያዩ ግብአቶች) እና የገበያ ትስስር በማመቻቸት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ ማህበራቱ የሚያመርቱት ምርት ዋነኛ ተጠቃሚ የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሲሆን፤ ከቢሮው ጋር ትስስር ተፈጥሮላቸው አንድ ኪሎ ግራም ኮምፖስት በ4 ብር ዋጋ ሲያቀርቡ መንግስት ደግሞ ዘርፉን ለማበረታታት የ3 ብር ድጎማ በማድረግ በድምሩ በ7 ብር እየሸጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የአረንጓዴ ቦታዎች አያያዝ፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፉ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፤ በከተማዋ በቢሮው አማካኝነት የለሙ 730 ሄክታር ስፋት ያላቸው አረንጓዴ ስፍራዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ለአረንጓዴ ዕፅዋት እድገትና እንክብካቤ ከሚያስፈልጉ ግብአቶች መካከል ኮምፖስት አንዱ ሲሆን በአረንጓዴ ልማትና እንክብካቤ የተሰማሩ 560 የሚሆኑ ማህበራት፣ ኮምፖስት ከሚያመርቱ ማህበራት የገበያ ትስስር ተፈጥሮ ኮምፖስት እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ከተማዋ የምታመነጨውን ቆሻሻ ለመልሶ መጠቀም እንዲውል ከማድረግ አኳያ አሁንም ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ያነሱት አቶ ሲሳይ፣ ለአረንጓዴ ስፍራዎች የሚያስፈልገው ኮምፖስት ወይም ማዳበሪያ ፍላጎት ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቆሻሻን ወደ ኮምፖስት በመቀየር በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እየተመረተ ያለው ኮምፖስት ለአረንጓዴ ልማት እንዲውል ከማድረግ ባሻገር በከተማዋ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮችም ለማቅረብ እንዲቻል ምቹ የመስሪያ ቦታ በማመቻቸት ረገድ እየተሰራ ነው፡፡ በዘርፉ የሚሰማሩ ማህበራት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በከተማዋ ከሚመነጨው ደረቅ ቆሻሻ ሊበሰብስ የሚችለውን ወደ ኮምፖስት መቀየር ከተቻለ ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ስራውን በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚከናወንበት ሁኔታ ለመፍጠር እንደ ጃፓንና ጋና ከመሳሰሉ ሀገራት ልምድ በመውሰድ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ በላይ ተናግረዋል፡፡ ደረቅ ቆሻሻን ወደ ሀብት በመቀየር በተለይ የሚበሰብሰውን ቆሻሻ ለኮምፖስት በማዋል ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ሆኖም በዘርፉ ካለው አቅም አኳያ ብዙ ስራ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ከመንግስት ባሻገር የግል ዘርፉንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር ይገባል፡፡  

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review