የአገልጋዩ አድራሽና መላሾች

You are currently viewing የአገልጋዩ አድራሽና መላሾች

  • 477 አውቶቡሶች የፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ

  • በመጪው 3 እና 4 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ቁጥራቸው ወደ 90 የሚሆኑ ተጨማሪ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎቱ እንደሚገቡ ተጠቁሟል

አንድም ቀን ካለምንም በቂ ምክንያት ከስራ ገበታቸው ቀርተው አያውቁም፤ ወይዘሮ መብራት ነጋሽ፡፡ ወይዘሮዋ ቦሌ አራብሳ በተለምዶ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሳይት ሶስት ነዋሪ ናቸው፡፡ ሁልጊዜ ከእንቅልፋቸው ሌሊት 9፡00 ሰዓት ላይ ይነሳሉ፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ለቀን ውሏቸው አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ ነው። ታድያ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ሰልፍ መያዣ ሰዓት ደረሰ አልደረሰ በማለት በጥድፊያ ከቤታቸው መውጣት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆኗል፡፡

መነሻውን ቦሌ አራብሳ ሰፈራ አድርጎ  እስከ ፒያሳ የሚወስደውን የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቡስ ለመያዝ ቢያንስ ሰልፍ ቦታው ላይ 10፡20 ሰዓት መድረስ እንደሚጠበቅባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ መብራት፤ ከቤት እስከ ሰርቪስ ቦታ ለመድረስ የሚጓዙት የእግር ጉዞ ጭንቅ ነው የሚሆንባቸው። “ጨለማው ለተለያዩ ችግሮች ያጋልጠን ይሆን” በሚል በስጋት ስሜት ውስጥ ሆነው ነው የሚጓዙት። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ሃይላንዶችን በቆሻሻ ማዳበሪያ እንለቅማለን” በሚል ዝርፊያ እና ድብደባ የሚያከናውኑ አካላት መኖራቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ይህንን መሰል ለአደጋ ያጋለጠ ክስተት ከዕለታት በአንዱ ቀን በእርሳቸውና በጓደኛቸው ላይ ሊደርስ አንዣቦ እንደነበረ አስታውሰው፤ የድረሱልን ጥሪ በማሰማታቸው ሰዎች መጥተው እንዳዳኗቸው ገልፀዋል፡፡

የወይዘሮ መብራት ነጋሽ እና የጓደኛቸውን ስጋት በመረዳት የቤተሰብ አባላት ሌሊት ላይ ወደ  አውቶብሱ መቆሚያ ድረስ እንደሚሸኟቸው የተናገሩ ሲሆን፤ እዚያ ከደረሱ በኋላ ሸኚዎች በሰላም ገቡ አልገቡ የሚለው በአንፃሩ ሌላ ስጋት እንደሚሆንባቸው ጭምር ገልፀዋል፡፡

ኮሎኔል ደምሴ ተሰማ ይባላሉ። ቦሌ አራብሳ (ሰፈራ) እስከ ፒያሳ የሚወስደውን የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶብስ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ሰርቪሱን መጠቀም ከጀመሩ አንድ ዓመት አስቆጥረዋል። ሰፈራ አካባቢ ያለው የትራንስፖርት ችግር እንዲቀረፍ ፊርማ በማሰባሰብ ቅሬታዎችን ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ተወክለው በአካል ሄደው እንዳመለከቱ ያነሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ፤ ያስገቡት የቅሬታ ማመልከቻ መፍትሔ ማግኘት አልቻለም፡፡ የእነሱን መስመር ይዘው የሚጓዙ የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶብሶች ከመነሻቸው ሞልተው እና በተሳፋሪ ተጨናንቀው ስለሚወጡ በየፌርማታው የሚገቡትን ለማስገባት ይቅርና ውስጥ ያለውን የተሳፋሪ ደህንነት የጠበቀ ጉዞ ለማድረግ አስቸጋሪ ስለመሆኑ ይናገራሉ።

የችግሩን መጠን ኮሎኔል ደምሴ እንዳስረዱት፤ “ጠዋት ሰርቪስ ለመያዝ በሚል ሌሊት መነሳት፣ የመውጫ ሰዓት ላይ ቀድሞ ከሥራ ወጥቶ መሰለፍ፣ አልፎ አልፎ በተፈጠረው መተፋፈግ በቀላሉ እንደ ጉንፋን ላሉ በሽታዎች ተጋላጭ መሆን የተለመደ ነው” በማለት ነው። ይህንን መሰል የሠራተኛውን ችግር የሚመለከተው አካል በማየት መፍትሔ ቢሰጥበት መልካም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ቤዛይት ተሾመ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ላለፉት 11 ዓመታት የመንግስት ሠራተኛውን በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ገልፀዋል። የመንግስት ሠራተኞች በአግባቡ በሥራ ገበታቸው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፤ ከወጪ አንፃርም በነፃ ለማጓጓዝ መቻሉ ትልቅ እፎይታን ስለመፍጠሩ አብራርተዋል፡፡ 

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱን በማስፋት የትራንስፖርት ተጠቃሚውን እርካታ ከመጨመር ባሻገር የተጠቃሚውን ቁጥር ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ በየጊዜው አገልግሎቱን ከማስፋት ባሻገር የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ትርፋማ የሚያደርጉ የተለያዩ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል። ታድያ በዋናነት ለተቋቋምንበት ዓላማ (የመንግስት ሠራተኛውን ጠዋትና ማታ ማጓጓዝ የሚለውን) ቅድሚያ ይሰጣል። የተሻለ አቅም ለመፍጠር በጎን ደግሞ ሌሎች ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን እንደሚሠራ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

“ተደራሽነቱን ከማስፋት አንፃር አሁን ላይ 477 አውቶቢሶችን ለዚሁ ዓላማ እየተጠቀምን እንገኛለን፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ የመንግስት ሠራተኛው የሥራ ቦታ በመቀየር ከመሀል ከተማ ወደ ማስፋፊያ ቦታ እየኖረ ይገኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በየጊዜው ተለዋዋጭ የሆኑትን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በየጊዜው መስመሮችን የመጨመር እንዲሁም የማራዘም ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል። ከዚህ ቀደም 50 የጉዞ መነሻዎች የነበሩ ሲሆን መዳረሻዎቻችንም ከ30 የማይበልጡ ነበሩ፡፡ በየጊዜው አውቶብሶቹ እየተጨመሩ ‘የመንግስት ሰራተኛው የት ነው የሚኖረው?’ የሚለውን ቦታ በመከታተል ስራችንን በስፋት ለመከወን ችለናል፡፡ በዚህ መሰረትም አሁን ላይ 113 የጉዞ መነሻዎች፤ 83 መዳረሻዎች አሉ” ሲሉ አብራርተዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት በማስፋፊያ አካባቢዎች በተለይ ለጽሑፋችን እንደ መነሻ ቅሬታዎች በተነሱበት አካባቢ ያለውን የትራንስፖርት እጥረት በተመለከተ ወይዘሪት ቤዛይት ሲናገሩ፣ “ባሉት አራት ቅርንጫፎች በተለይ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅ እንዲሁም በምዕራብ የሚገኙ መስሪያ ቤቶቻችን በየጊዜው ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? ስንል ሪፖርቶችን እንቀባበላለን። ለመፍትሔውም አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል፡፡ በተለይ ከ2016 ዓ.ም በኋላ የትራንስፖርት ስምሪት አለመረጋጋት መፈጠር የጀመረበት ጊዜ ነው፡፡ ለዚህ የነዋሪዎች ቁጥር መጨመር እንዲሁም የተቋማት የስራ ቦታ መቀያየር ከምክንያቶቹ መካከል ናቸው” ሲሉ አንስተዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ በምስራቅ ቅርንጫፍ ስር የሚገኘው ቦሌ አራብሳ በተለምዶ ሰፈራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በአንድ አውቶቢስ ነበር፤ አሁን ላይ ቁጥሩ ጨምሮ አራት ደርሷል። ይህ ማለት ግን ከተደራሽነት አንፃር በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር ጊዜያዊ መፍትሔ ለማበጀት ያክል ስምሪት የበዛባቸውና ያነሰባቸውን የአውቶቢስ ስምሪቶችን በማጤን አስፈላጊ ወደሆኑ ስፍራዎች የመመደብ አግባብ አለ፡፡ ቆጠራ በማድረግ መዳበል የሚችሉ መስመሮችን በማንሳት ችግሩ ወደባሰባቸው አካባቢ አውቶብሶችን የመመደብ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በየሦስት ወሩ ተጠቃሚዎቻችንን በምናዘጋጀው መድረክ ላይ የማግኘት ስራ እየተሰራ ነው። ችግሮች አሉ በሚሏቸው ቦታዎች ላይ ጥያቄያቸውን በማንሳት እዩልን ይላሉ፡፡ በቀን በቀንም የሱፐር ቪዥን ሰራተኞች ታች ድረስ በመውረድ ተጠቃሚዎችን ያነጋግራሉ፡፡

“ብዙ ተሳፋሪ የሌላቸውን መስመሮች እያየን እየቆጠርን ብዙ ስምሪት በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ ደግሞ የአውቶብሶችን ቁጥር የመጨመር ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፡፡ እነዚህን ሁሉ ስራዎች ስንሰራ የተገልጋዩን እርካታ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ችለናል ብሎ ለማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ባለን ውስን ሃብት መሰረት አስፈላጊውን መፍትሔ ለመስጠት እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

እንደ ወይዘሪት ቤዛይት ገለፃ፤ በዘላቂነት ችግሮችን ለመፍታት አውቶቡሶችን ገዝቶ ማምጣት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን በመረዳት ዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ የማውጣት ስራ ተሰርቷል፡፡ ህጋዊ ሂደቱን አልፎ አሁን ላይ ከጨረታው አሸናፊ ጋር  ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ በማውጣት ግዢ ለመፈጸም ውል ገብተናል፡፡ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠትም  ከ3 እስከ 4 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ  90 አውቶቡሶች የሚገቡ ይሆናል፡፡ ይህ በትንሹም ቢሆን ያለውን መጨናነቅ ለመቅረፍ የሚቻልበት አግባብ ይፈጥራል፤ የተገልጋይን ቅሬታም ይፈታል፡፡ በቀጣይም የገቢ ምንጩን በማሳደግ ተጨማሪ አውቶቡሶችን በየዓመቱ የመግዛት እቅድ አለ፡፡ አሁን ካለውም በላይ የመንግስት ሰራተኛውን የሚመጥን ስራ ይሰራል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ስራውን በሚፈለገው ልክ ለመስራት እንዳይቻል እንቅፋት የሆኑትን ሲዘረዝሩ፣ “ለቁጥጥር ሲወጣ ህገ ወጥ መታወቂያዎችን የሚጠቀሙ ተሳፋሪዎች በብዛት ይገኛሉ። ለዚህም እንደ መፍትሔ የተወሰደው ከሸገርና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመሆን ድንገተኛ ፍተሻዎችን ማድረግ ነው። በቀን ውስጥ ከ50 እስከ 60 ህገ ወጥ መታወቂያዎች የያዙ  ተሳፋሪዎች ይገኛሉ። በዚህ ደግሞ ትክክለኛውን የመንግስት ሰራተኛ ተጠቃሚ ለማድረግ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ለዚህም እንደመፍትሔ የተወሰደው የዲጂታል መታወቂያን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የወረቀት መታወቂያን ማስቀረት ዋነኛ ዓላማችን በማድረግ ህገ ወጥነትን መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስራ መስራት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ቁጥራቸው ወደ 90 ሺህ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች መረጃዎቻቸው ተሞልቷል” ብለዋል፡፡ ቁጥራቸው 27 ሺህ የሚሆኑ የአዲስ አበባ እና ከ96 ሺህ በላይ የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች የፐብሊክ ሰርቪስ ተጠቃሚ መሆናቸውን አክለዋል።

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review