ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ፣ የሀገርን ገፅታ ለማሳደግ፣ ለኢኮኖሚ እና ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ባለሀብቶች እና የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ይህን ውሳኔ ተከትሎ ከባለሀብቶች እና ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተዋናዮች ጋር በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ የሀገርን ገፅታ ለማሳደግ፣ ለኢኮኖሚ እና ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ከኦሜዳድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቶ አባተ ባዬ፣ መርሐ-ግብሩ ኢትዮጵያ ያላትን ታሪካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ብቃት እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነት ለማሳየት የሚያስችል ትልቅ አጋጣሚ ብለዋል።

ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩኘ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፣ ይህ ጉባኤ ሀገርን በዓለም አደባባይ ከፍ የሚያደርግ እና ለአጭር ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም እንደ ኦሊምፒክ ያሉ ሌሎች ትላልቅ ዝግጅቶችን የማስተናገድ ዕድል በር ይከፍታል።
ከጊፍት ሪል ስቴት አቶ ገብረኢየሱስ ኢጋታ፣ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ይበልጥ መነቃቃት ለመፍጠር ጉባኤው በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
አቶ በላይነህ ክንዴ እንደተናገሩት፣ ጉባኤው ኢንቨስትመንትን ያሰፋል፣ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የቱሪዝም ዘርፉን ከፍ ያደርጋል እንዲሁም ብዙ ዶላር እና ገቢ ወደ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያመጣል።

ኢትዮጵያ ጉባኤውን እንድታዘጋጅ መመረጧ የመንግስት የዲፕሎማሲ ውጤት፣ የህዝብ ድካም እና ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ያደረገችው አስተዋፅኦ መገለጫ ነው ብለዋል።
ባለሀብቶቹ በሚሰጡት አገልግሎት ላይ ሰፋ ያለ ዝግጅት ለማድረግ እና ጉባኤው በሚያስፈልጉት ጉዳዮች ሁሉ የበኩላቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።
በሔለን ተስፋዬ