ዛሬ ማለዳ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች፣ አራት G+4 የማምረቻ እና መሸጫ ህንፃዎችን ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ሲሰሩ ለነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ማስረከቡን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች 976 አንቀሳቃሾች ሲሆኑ፣ በ292 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ ተደርጓል።
የከተማ አስተዳደሩ በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት በመለወጥና ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችሉ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ520 ሺህ በላይ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር መቻሉንም ነው ከንቲባ አዳነች በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት የገለፁት።
ተጠቃሚዎች፣ የተፈጠረላቸውን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆነው ስላየንም እጅግ ደስተኞች ነን ብለዋል ከንቲባ አዳነች።
ከንቲባ አዳነች አክለውም “ዛሬ ያስረከብናችሁ የመስሪያ ቦታ ነገ የእናንተ እህቶች፣ ወደፊትም ወንድሞችና ልጆች ተረክበው የሚሰሩበት መሆኑን ተገንዝባችሁ በኃላፊነት ልትጠቀሙበት ይገባል”ብለዋል።
በቀጣይም በስልጠና ያገኙትን ክህሎት በስራ ህይወታቸው በመተግበር በርትተው የበለጠ ውጤታማ በመሆን ሌሎችም የእነሱን መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ከንቲባ አዳነች ባሰፈሩት መልዕክት ገልፀዋል።