ኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በታላቅ ፈተና ውስጥ ሆና ያስመዘገበቻቸው ሁሉን አቀፍ ስኬቶች ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ የሚያስቀራት ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማ የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች በሚል መሪ ሐሳብ ህዝባዊ ውይይት እየተካሔደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ አመታት በታላቅ ፈተና ውስጥ ሆና በርካታ ስኬቶችን ተቀዳጅታለች ብለዋል።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጉጉትና ትብብር ታረፈበት የህዳሴ ግድብ የገጠሙትን ችግሮች በመፍታት የዘመናት የህዝብን ቁጭት ወደ ሐሴት መቀየር መቻሉን አንስተዋል ።

ኢትዮጵያ የምግብ ሉአላዊነቷን ለማረጋገጥ በስንዴ ምርት በተሰራው ስራ ከራስ አልፎ ለውጪ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልፀዋል ።
በገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች በተሰራው ስራ የሀገሪቱን እምቅ የቱሪዝም አቅም ማነቃቃት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ለዘመናት ያልተጠቀምንባቸውን ነዳጅን ጭምሮ ከፍተኛ የማእድን ሃብቶቻችንን በአግባቡ መጠቀም ጀምረናል ብለዋል ።
በአረንጓዴ አሻራ፣በከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት አለም አቀፍ እውቅናን ያተረፉ ስራዎችን ማሳካት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ሆና ያስመዘገበቻቸው በርካታ ተግባራትና ስኬቶች ከጀመረችው የብልጽግና ጉዞ የሚያስቀራት ምድራዊ ኃይል እንደሌለለ ማሳያ ነው ብለዋል።
በሄኖክ ዘነበ