የሥነ-ጥበብ ፈጠራ ስራዎችን ገዥ ትርክትን ለማስረጽና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሀት ገለጹ።

በኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ የተዘጋጀ የጥበባትና ፈጠራ ኢንዱስትሪ የምክክር መድረክ በመካሄድ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻህፍት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሀት፤ ሥነ-ጥበብ እና ሀገረ መንግስት በሚል የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በዚህም ሥነ-ጥበብ ረቂቅ ሰብዓዊ ስሜቶች በትዕምርት የሚቀረጽበት ፈጠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲሁም ማህበራዊ እውነታን በምስል የሚያንጸባርቅ እና ሰዎች ስለዓለም ያላቸውን ውበታዊ ግንዛቤ የሚገልጽ ክዋኔ መሆኑን ተናግረዋል።

ሥነ-ጥበብ ተደራሲን ወይም የአድናቂን አእምሮ የመቆጣጠር እና ለገሀዱ ዓለም ከሚሰጠው ትርጉም በላቀ በምናብ ለተፈጠረው ጉዳይ ቀልቡን እንዲሰጥ ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችል ጥበብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሀገራትን አጽንቶ ያቆመ ትልቅ ቁም ነገር ገዥ ትርክት መሆኑን ጠቁመው፤ ነጠላ ትርክት ኢትዮጵያን በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድትገባ ማድረጉን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ኢትዮጵያዊነት የደም ስሩ መሆኑን ገልጸው፤ ገዥ ትርክትን ለማጽናት መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የክልል የባህልና ስፖርት ቢሮ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።