በኢትዮጵያ 2ኛ የሆነዉ የጅማ ዓይን ባንክ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

You are currently viewing በኢትዮጵያ 2ኛ የሆነዉ የጅማ ዓይን ባንክ ማዕከል ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
  • Post category:ጤና

AMN ታህሣሥ 04/2018 ዓ.ም

ከአዲስ አበባ አይን ባንክ ቀጥሎ 2ኛ የሆነዉ የጅማ ዓይን ባንክ ማዕከል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ መንግሥት የጤና አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዉ በተለይም ደረጃዉን የጠበቀ የህክምና መስጫ ማዕከላትን በማስፋፋት የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ብሎም በሀገሪቱን የሜዲካል ቱርዝምን ለማሳደግ የተያዘዉን ግብ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

ለዓይን ህክምና አገልግሎት መሻሻል መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ያሉት ዶ/ር ደረጀ በየደረጃዉ ያለዉ አመራርና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው የዓይን ብሌን ለጋሾች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ከዚህ በተሻለ መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክረዉ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ በመግለጽ በቀጣይም የዓይን ባንክ አገልግሎት ወደ ክልሎች እንዲስፋፋ ይሰራል ብለዋል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ፕሮፈሰር ነፃነት ወርቅነህ በበኩላቸዉ የጅማ የዓይን ባንክ አገልግሎት በጅማ መከፈቱ ለጅማና አከባቢዉ ማህበረሰብ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለጎረቤት ሀገራትም ጭምር ትልቅ ተሰፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከጅማ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አገልግሎቱ ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊዉን ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ማለታቸዉን የጤና ቢሮ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review