በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በያዝነው በጀት ዓመት ከተለያዩ ወረዳዎች የተሰበሰቡ ከ22 ሺህ በላይ የሺሻ ማስጠቀሚያ እቃዎች መወገዳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከክፍለ ከተማው ሠላምና ፀጥታ አስተዳድር ጽ/ቤት እና ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ቤት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ወራት በክፍለ ከተማው ስር በሚገኙ ወረዳዎች በተሰራው ኦፕሬሽን የተሰበሰቡ 22 ሺ 750 የሺሻ ማስጠቀሚያ እቃዎች ተወግደዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር በኃይሉ ደጀኔ እንደተናገሩት በክፍለ ከተማው ስር ከሚገኙ አራት ወረዳዎችና የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ወራት የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ በፔሲዮን፣ ቪላ ቤት፣ ጭፈራ ቤት እና ለዚህ አገልግሎት በሚውሉ መኖሪያ ቤቶች ላይ በተሰራ የኦፕሬሽን ስራ የተሰበሰቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት የሚያውኩ ወንጀል ፈጻሚዎች የወንጀል እቅዳቸውን የሚያወጡበት ስፍራን ማስወገድ ማለት ወንጀል እንዳይፈጸም ምቹ ሁኔታ በማሳጣት ሠላም የማረጋገጥ ስራ መሆኑን ኮማንደር በኃይሉ ደጀኔ ገልጸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታዬ ሽፈራው ወንጀል ፈጻሚዎች ድፍረት እንዲሰጣቸው ሺሻዎችን በመጠቀም ወደ ወንጀል የሚገቡበትና የህብረተሰቡን ሠላም የሚያውኩበት የወንጀል መንስኤ የሆኑ ነገሮችን በማስወገደ ህብረተሰቡ እፎይ እንዲል የተደረገበት ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሺሻ ማስጠቀም ጋር በተያያዘ 209 ግለሰቦች ላይ 105 የምርመራ መዝገቦችን በማደራጀት በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል።