ብልጽግና ፓርቲ ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የተካሄዱ ህዝባዊ የወይይት መድረኮችን አስመልክቶ ‘ብልፅግና ህዝብን ያዳምጣል፤ ችግርን ይፈታል’ ሲል መግለጫ አዉጥቷል።
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ቃል ህዝባዊ የውይይት መድረኮች እያካሄደ ይገኛል፡፡
ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በመዲናችን አዲስ አበባ አስራ አንዱም ክ/ከተሞች እና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች የውይይት መድረኮች ከፍ ያለ የህዝብ ተሳትፎ የታየባቸው ሆነው ተካሂደዋል፡፡
መድረኮቹ እስካሁን በፓርቲና መንግሥት የበላይና ከፍተኛ አመራር አወያይነት በ24 ከተሞች ተከናውነዋል፤ በቀጣይም ወደ ተለያዩ ከተሞችና ገጠር አካበቢዎች የሚወርድ ሲሆን መላ ህዝባችን የውይይት መድረኩ አካል ሆኖ ይሳተፋል፡፡
ህዝባዊ የውይይት መድረኮቹ መንትያ ግቦች ያነገቡ ናቸው፤ አንደኛው ግብ ብልፅግና ለህዝብ የገባውን ቃል ህዝብ አስተባብሮና ተጠቃሚ አድርጎ በተግባር የገለጠበትን እውነታ ከህዝቡ ከራሱ አብሮ ለመገምገም ነው፤ ሁለተኛው ግብ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የሚሰተዋሉ ችግሮችን ከህዝቡ ከራሱ በማዳመጥ መፍትሄ መስጠት ነው፡፡
እነዚህ መንትያ ግቦች ያነገበው ህዝባዊ የውይይት መድረክ በያዝነው ዓመት መባቻ ከኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ምርቃት ጋር ተሰናስነው የተበሰሩትን 7ቱ የጉባ እና የመደመር መንግሥት ብስራቶች ዋቢ አድርጎ መሪ ቃሉን መርጧል፡፡

የህዝባዊ ውይይት መድረኩ መሪ ቃል አካል የሆነው አንደኛው ነጥብ 7ቱ የጉባ ብስራቶች ሲሆኑ እነዚህም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክታችን በድምር በ6 እጥፍ ሚተልቁ የ30 ቢልየን ዶላር ፕሮጆክቶች ናቸው፡፡
እነዚህ የማዳበሪያ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የጋዝ ኃይል፣ የኒኩሌር ኃይል፣ የቤት ልማት እና የግዙፍ አየር ማረፍያ ግንባታ ፕሮጆክቶች ኢትዮጵያን በቀጣይ 5 ዓመታት ወደ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የሚያደርሱ እና የሀገረ-መንግስት ግንባታ አካል የሆኑ ስትራቴጂክ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
ታላቁ ህዳሴ ግድባችንን “ዳግማዊ ዓድዋ” ብለን እንድንሰይመው እንዳስቻለን ሁሉ እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ “ሳልሳዊ ዓድዋ” ተብለው የመሰየም ዕድል ያላቸው ትላልቅ ሀገራዊና አሁጉራዊ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
ፕሮጀክቶቹ ከ5 ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ከኢኮኖሚያዊ ነጻነት፣ ከሥራ ዕድልና ሀብት ፈጠራ የተያያዙ ትላልቅ ዝላዮች እንደሚፈጠሩበት ይጠበቃል፡፡
የህዝባዊ ውይይት መድረኩ መሪ ቃል አካል የሆነው ሁለተኛ ነጥብ የመደመር መንግሥት ነው፡፡ የመደመር ዕሳቤ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እዉን ለማድረግ የሀገራዊ ለውጡ መሪ ዕሳቤ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡
ዕሳቤው በተግባር መሬት ላይ ወርዶ ኢትዮጵያን ከተስፋ ብርሀን ወደ ሚጨበጥ ብርሀን ማሸጋገር ችሏል፡፡ በዚህ ተጨባጭ ለውጥ መነሻነት መደመር ከዕሳቤነት ወደ መንግሥትነት ተሸጋግሯል፡፡
በዚህ ደረጃ በልማቱም በሀገረ-መንግሥት ግንባታውም ለህዝብና ሀገር የሚመጥን ሥራ የሰራውና እመርታ የፈጠረው የመደመር መንግሥት በነቂስ ወጥቶ ከመረጠው ህዝብ ጋር ተገኛኝቶ እየተወያየ ነው፡፡

በውይይቱም የቀጣይ 5 ዓመት ህዝባዊ ዕቅዱ ላይ አተኩሮ “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች” በማለት ትሩፋቶቹን ከህዝብ ጋር እየተቋደሰና ተስፋውን እያለመለመ ይገኛል፡፡
በህዝባዊ ውይይት መድረኮቹ በሰፊው የተስተዋለው አንድ ጉዳይ ህዝብ የተሰራለት ሥራ ቆጥሮ የሚያውቅና የሚያመሰግን መሆኑን ነው፡፡
በሁሉም መድረኮች ባለፉት 5 እና 7 ዓመታት የተሰሩት የልማት እና የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሥራዎች በህዝቡ አንደበት በአድናቆትና በምስጋና ታጅበው ቀርበዋል፡፡
ህዝቡ በየዘርፉና በየአከባቢው የተሰሩ አያሌ ሥራዎች እንዲሁም በቀጣይ 5 ዓመታት የሚሰሩ መደበኛና ታላላቅ ፕሮጀክቶች የላቀ ተስፋ እንደፈጠሩለት አሳይቷል፡፡
በህዝባዊ ውይይቱ ባለፉት 5 ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ማለትም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በዓለምአቀፍ ዘርፎች አያሌ ድሎችና እመርታዎች መመዝገባቸውን አንስቷል፡፡
በፖለቲካ ረገድ የፖለቲካ ምህዳሩ ከማስፋትና ከማዘመን ጋር የተያያዙ ሥራዎች ተሰርተው በሀገራችን የትብብርና የፉክክር ሚዛን የጠበቀ ፖለቲካ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
በዚህም 275 የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራር (ከነዚህም 7ቱ በሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ) የተለያዩ መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ይዘው እየመሩ ይገኛሉ፡፡
በኢኮኖሚ ረገድ በብዝሀ-ዘርፍና ብዝሀ-ተዋንያን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በመመራት በምርትና ምርታማነት ከፍተኛ እመርታ መጥቷል፡፡
በግብርና (በተለይ በስንዴ፣ በቡናና በሌማት ቱርፋት)፣ በአምራች ኢንዳስትሪ፣ በማዕድን እና በቱሪዝም የመጡ ለውጦች የነበሩ የሥርዓት ስብራቶችን የጠገኑ ብቻ ሳይሆኑ ሽግግር የፈጠሩ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
በማህበራዊ ረገድ ሰው ተኮር ፖሊሲዎች ተተግብረው ህዝባዊ ክብርን እስከመጎናጸፍ የደረሱ አያሌ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከተረጂነት ሙሉ ለሙሉ ከማላቀቅ እስከ ማህበራዊ ዋስትና የሚያረጋግጡ የትምህርትና የጤና ተጨባጭ ለውጦች ተፈጥረዋል፡፡
በዓለምአቀፍ ግንኙነት ረገድ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ፣ ከአይናፋርነት የተላቀቀ እና ጥበብና ድፍረት በተሞላው አካሄድ ተፈጥሮ ሀብቶቻችን ጨምሮ ታሪካዊው የባህር በር ጥያቄያችን ዓለም በፍትሀዊነት የደገፈው አጀንዳ ማድረግ ተችሏል፡፡

ዜጋ-ተኮር የሆነ፣ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ፣ ቀጠናዊ ትስስርን የሚፈጥር እና ዓለምአቀፍ ትብብርን የሚደግፍ የውጭ ፖሊሲ በመተግበር የኢትዮጵያ ተሰሚነትና ቅቡልነት ከፍ ያደረጉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡
መንግሥት በነዚህና ሌሎች አያሌ ድሎች ሳይዘናጋና ሳይኩራራ በህዝብ ዘንድ የሚነሱ ችግሮችና ቅሬታዎች በመድረኩ እንዲነሱ አድርጓል፡፡
መንግሥት በህዝብ ዘንድ የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ከህዝቡ አንደበት ለማዳመጥ የሄደበት ርቀት የህዝባዊነቱ እና የአገልጋይነቱ ጥግ ማሳያ መሆናቸው በተሳታፊዎች በደስታ-እምባ ጭምር የታጀበ እውቅናና ምስክርነት ተሰጥቶታል፡፡
ይህ ነባራዊ ሁኔታ በአንዳንድ ባዳዎችና ባንዳዎች በማህበራዊ ሚዲያ ከሚነዙ የሀሰት ወሬዎችና አሉባልታዎች በተቃራኒ ህዝብ ከመንግሥት ጎን ያለ መሆኑ እና የሚያጋጥሙ ችግሮችም ከመንግሥትና ህዝብ የመፍታት አቅም በላይ አለመሆናቸው ከፍተኛ እምነትና ተስፋ እንዳለ ታይቷል፡፡
የመንግሥት ህዝባዊነትና ህዝብን የማዳመጥ ተግባር በተከታታይ ዓመታት የተስተዋለ ቢሆንም በዚህ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ውይይት ላይ የተለየ ትርጉም ተገኝቶበታል፡፡
ይህ የተለየ ትርጉም በዚህ ዓመት ነጻ፣ ፍትሀዊ፣ ተዓማኒና አሳታፊ ሆኖ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲሁም ለቀጣይ 5 የብልፅግና የመሪነት ዓመታት ያለው ህዝባዊ ድጋፍና ዝግጁነት ነው፡፡
የመደመር መንግሥት በህዝብ የለውጥ ፍላጎት ወደ መሪነት የመጣ ህዝባዊ መንግሥት እንደመሆኑ መጠን በቀጣይም ከህዝብ ለህዝብ እና በህዝብ በሆነ የለውጥ መርህ መሪነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በመደመር ዕሳቤ የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ እና የመደመር መንግሥት ይህንን የታደሰ ህዝባዊ እምነትና ተስፋ እንደተጨማሪ አደራ በመቀበል ኢትዮጵያ በታሪክዋ እና ማደግ በሚገባት አቅም ልክ ወደ ብልፅግና ማማ ለማድረስ የሚደረገው ርብርብ ያጠናከራል፡፡