የግል ተበዳይ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን በመጠቀም በሰጡት ጥቆማ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing የግል ተበዳይ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን በመጠቀም በሰጡት ጥቆማ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN – ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም

በተመሳሳይ ቁልፍ የተሽከርካሪያቸው በር ተከፍቶ ሠነድ የተሰረቀባቸው ግለሠብ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp በመጠቀም በሠጡት ጥቆማ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

ተከሳሾቹ ወንደሠን ድንበሩ እና መኩሪያ ቢሆነኝ የተባሉ ሲሆን የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አካባቢ ነው።

የግል ተበዳይ መኪናቸውን አቁመው በሄዱበት አጋጣሚ ተከሳሾቹ በተመሳሳይ ቁልፍ በሩን ከፍተው ከተሽከርካሪው ውስጥ የቤት ካርታና የባንክ ቼክ እንዲሁም ሌሎች ሰነዶችን ሰርቀው ይሰወራሉ።

የግል ተበዳይ ተሽከርካሪያቸው ተከፍቶ ሰነዶቹ እንደተሰረቁባቸውና ተጠርጣሪዎቹም ስልክ ደውለው በአስቸኳይ 50ሺህ ብር እንዲያስገቡ ካላስገቡ ሰነዶቹን እንደሚያጠፉባቸው ይነግሯቸዋል።

የግል ተበዳይ ይህ ወንጀል ከተፈጸመባቸው በኋላ ካሉበት ቦታ ሆነው የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ Citizen Engagement Application በመጠቀም መረጃውን ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል።

በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የአለም ባንክ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የግል ተበዳይን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ተከሳሾቹን ለመያዝ ባደረገው ጥረትና ምርመራ 3 ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቱንም ተከሳሾች በልደታ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ከክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ግለሰቦቹ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ቁልፍ የመኪና በር በመክፈት ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ሲፈፅሙ የነበረ ሲሆን አስፈላጊውን ምርመራ በማጣራትም በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ተገልጿል።

ተሽከርካሪ አቁመው የሚሄዱ ግለሰቦች አስተማማኝ ጥበቃ ባለበት ቦታ መሆን እንዳለበትና በተሽከርካሪው ውስጥ የሚቀመጡ ንብረቶችም ከወንጀለኞች እይታ ውጭ መቀመጥ እንዳለባቸው ያሳሰበው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ወንጀል ሲፈፀምም በቀላሉ የተንቀሳቃሽ ስልክን በመጠቀም በፌዴራል ፖሊስ የለማውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያ (citizen engagement application) ላይ መረጃውን በመስጠት ማመልከት እንደሚገባም ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ መልዕክት አመላክቷል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review