በማንችስተር ዩናይትድ ተገፍቶ በኦሊምፒክ ማርሴ የፈካዉ ግሪንዉድ

You are currently viewing በማንችስተር ዩናይትድ ተገፍቶ በኦሊምፒክ ማርሴ የፈካዉ ግሪንዉድ

AMN ታኅሣሥ 06 ቀን 2018 ዓ.ም

የተወለደው በእንግሊዝ ብራድፎርድ ነው፡፡ ገና በስድስት ዓመቱ ነበር የማንችስተር ዩናይትድ አካዳሚን የተቀላቀለው፡፡ 11 ዓመታትን በአካዳሚው ካሳለፈ በኋላ በ2018 ወደ ዋናው ቡድን አደገ፡፡

ጥር 2022 መጥፎ ዜና ተሰማ፡፡ ሜሰን ግሪንዉድ እጮኛው ላይ ጥቃት ፈፅሟል ተብሎ ክስ ተመሰረተበት፡፡

በዚህ የተነሳ የክለቡ ደንብና መመሪያ ጥሷል፣ ለታዳጊ ተጨዋቾች አርአያ አይሆንም ያለው ማንችስተር ዩናይትድ ጥር 30 2022 ከክለቡ አገደው፡፡

በቀረበበት ክስ ላይ ሲከራከር የቆው ግሪንዉድ ዘግይቶም ቢሆን ከክሱ ነጻ ወጣ፡፡ ከእጮኛው ጋር ተጋብቶ ልጅ ቢያፈራም የጠለሸውን ስሙን ማደስ ግን ቀላል አልሆነለትም፡፡

ቡድኑን እንዲቀላቀል ያልፈለገው ማንችስተር ዩናይትድ በ2023 የውድድር ዓመት ለስፔኑ ሄታፌ በውሰት ሰጥቶት ተጫውቷል፡፡

በውሰት ቆይታው ለላሊጋው ክለብ 33 ጨዋታዎችን አድርጎ 8 ግቦችን ከመረብ አሳረርፏል፡፡

የውሰት ጊዜው እንደተጠናቀቀ ወደ ዩናይትድ ቢመለስም ክለቡ በቋሚ ዝውውር የሚገዛውን አፈላለገ፡፡በመጨረሻም የፈረንሳዩ ኦሊምፒክ ማርሴ በ31 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ የግሉ አደረገው፡፡

በፈረንሳዩ ክለብ የሁለተኛ ዓመት ውድድሩ ላይ የሚገኘው የ24 ዓመቱ ግሪንዉድ በሊግ አንድ ታሪክ እየሰራ ይገኛል፡፡

በ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ትናንት ምሽት ኦሊምፒክ ማርሴ ጠንካራውን ሞናኮ 1ለ0 ሲያሸንፍ ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ግሪንዉድ ነው፡፡

ከፔሬ ኤምሪክ ኦባሚያንግ ጎን የሚሰለፈው ተጫዋቹ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን የሊግ አንድ ግቦች 11 አድርሶ እየመራ ነው፡፡

ግሪንዉድ የወርቅ ጫማውን ለማሸነፍ ከተከታዩ ኢስቴባን ሊፓውል በአራት ግቦች ይበልጣል፡፡

ኦሊምፒክ ማርሴ ካደረጋቸው 16 የሊግ አንድ ጨዋታዎች 10 አሸንፎ ፣ ሁለት አቻ ወጥቶና አራት ጨዋታዎችን ተሸንፎ በ32 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ሎንስ በ37 እና ፒ ኤስ ጂ በ36 ነጥብ ከማርሴይ በላይ ያለውን ደረጃ የያዙ ክለቦች ናቸው፡፡

በማንችስተር ዩናይትድ ዋናው ቡድን ስድስት ዓመታትን ሲያሳልፍ 83 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ሜሰን ግሪዉድ ፣ ፈረንሳይ ከደረሰ በኋላ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ በ49 ጨዋታዎች 32 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡

ለእንግሊዝ ከ15 ፣ ከ17 ፣ ከ18 እና ከ21 ዓመት በታች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ለእንግሊዝ ዋናው ቡድን አንድ ጨዋታ ብቻ ያደረገው ግሪንዉድ ለእናቱ ሀገር ጃማይካም የመጫወት እድል አለው፡፡

ገና በ21 ዓመቱ ስሙ ከመጥፎ አጀንዳ ጋር የተያያዘበት ግሪንዉድ በእንግሊዝ ካሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ ተላቆ በፈረንሳይ ሊግ አንድ እንደ አዲስ ተወልዷል፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review