ማንችስተር ዩናይትድ ደረጃውን ለማሻሻል ቦርንማውዝን ይገጥማል

You are currently viewing ማንችስተር ዩናይትድ ደረጃውን ለማሻሻል ቦርንማውዝን ይገጥማል

AMN ታኅሣሥ 06 ቀን 2018 ዓ.ም

የ16ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር ዛሬ ማንችስተር ዩናይትድ እና ቦርንማውዝ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጠናቀቃል።

ማንችስተር ዩናይትድ ከመጨረሻ ዘጠኝ ጨዋታዎች የተሸነፈው አንዱን ብቻ ቢሆንም ወጥነት ይጎለዋል።

በተለይ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ያደረጋቸው የኤቨርተን እና ዌስትሃም ጨዋታ ላይ አንድ ነጥብ ብቻ ማግኘቱ ደጋፊዎችን አበሳጭቷል።

ዛሬም በሜዳው ከቦርንማውዝ ጋር ሲፋለም ተመሳሳዩ እንዳይፈጠር ስጋት አላቸው።

በተለይ ቦርንማውዝ ሁለት ተከታታይ ዓመት ማንችስተር ዩናይትድን በገዛ ሜዳው በተመሳሳይ 3ለ0 ማሸነፉ የዛሬውም ጨዋታ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።

በእርግጥ ቦርንማውዝ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ የነበረው ብርታት አብሮት የለም። ከስድስት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎቹ ምንም ዓይነት ድል አልቀመሰም። አራቱን ተሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።

በዛሬው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ብሪያን ምቡሞ ፣ አማድ ዲያሎ እና ኑሰይር ማዝራዊ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከማቅናታቸው በፊት የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በጉዳት ለሳምንታት ከሜዳ የራቀው ቤንጃሚን ሼሽኮ ወደ ልምምድ ቢመለስም ለዛሬው ጨዋታ መድረሱ አልተረጋገጠም።

ተከላካዮቹ ሀሪ መጓየር እና ማቲያስ ደሊግት ለጨዋታው እንደማይደርሱ አሰልጣኙ ሩበን አሞሪም አረጋግጧል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ድል ከቀናው ነጥቡን 28 በማድረስ ወደ 5ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ይችላል።

ዋና ዳኛ ሳይመን ሁፐር የሚመሩት የምሽቱ ጨዋታ 5 ሲል ይጀምራል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review