ከፒያሳ አከባቢ በልማት ምክንያት ለተሻለ ኑሮ ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሄዱ ነዋሪዎች የቀድሞ መንደራቸውን ፒያሳ አራዳ ፓርክን እና አከባቢውን ጎብኝተዋል

You are currently viewing ከፒያሳ አከባቢ በልማት ምክንያት ለተሻለ ኑሮ ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሄዱ ነዋሪዎች የቀድሞ መንደራቸውን ፒያሳ አራዳ ፓርክን እና አከባቢውን ጎብኝተዋል

AMN- ታኅሣሥ 06/2018 ዓ.ም

ከፒያሳ አከባቢ በልማት ምክንያት ለተሻለ ኑሮ ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሄዱ ነዋሪዎች የቀድሞ መንደራቸውን ፒያሳ አራዳ ፓርክን እና አከባቢውን ጎበኙ።

በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው መመልከታቸውን እና በአከባቢያቸው የተሰሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ነዋሪዎቹ ለልማት የተነሱበት የቀድሞ መንደራቸውን እንዴት እንደለማ እንዲጎበኙ እንደሚያመቻቹ በገቡት ቃል መሰረትም ነዋሪዎቹ ጉብኝት አካሂደዋል።

አራዳ ፓርክ በ42 ሄክተር መሬት ላይ ያረፈና በውስጡ የስፖርት አሬና፣ የልጆች መጫዎች ስፍራዎች፣ አንፊ ቲያትሮች፣ የስብሰባ አደራሾች፣ የመኪና መቆሚያዎች፣ ሱቆች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች፣ የመሮጫ ትራኮች፣ የብስክሌት መንገዶችን ጨምሮ አንድ ትንሽ ከተማ ሊኖራት የሚችል መሰረተ ልማቶችን በአንድ ቦታ አካቶ የተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻና እና የኮሪደር ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከድር አደም በጉብኝቱ አብራርተዋል።

ጎብኝዎቹ ከዚህ በፊት ይኖሩበት የነበረው ይህ ስፍራ በኮሪደር ልማቱ እጅግ ተቀይሮ በማየታቸው እንዲሁም የልማቱ አንድ አካል እና ተጠቃሚም በመሆናቸውን መደሰታቸውን ገልፀዋል።

አካበባቢው ከዚህ በፊት ለኑሮ ምቹ እንዳልነበር ያስታወሱት ጎብኝዎቹ ከተማ አስተዳደሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ያመቻቸላቸው መኖሪያ ቦታ እና በአከባቢው የተሰሩ የልማት ስራዎች ኑሯቸውን ቀላል እዳደረገላቸው ተናግረዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ካባ መብራቱ ከፒያሳ አከባቢ በልማቱ ተነስተው ወደ ክፍለ ከተማቸው የመጡ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት ከማመቻቸት ጀምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላቸው ምቹ መኖሪያ መንደር መመስረታቸውን ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በላይ ደጀን በአራዳ ፓርክ የተሰሩ የልማት ስራዎች የሀገርን መልካም ገፅታ የሚገነቡ፣ አዲስ አበባን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት መሆኗን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

ከተለያዩ አከባቢዎች ተነስተው ውደ ሌላ ቦታ የገቡ ነዋሪዎች በቀጣይ በተነሱበት አከባቢ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቢሮ ሀላፊው ጠቁመዋል።

ወጣቶች፣ የስፖርት ቤተሰቦች እና ሌሎችም ነዋሪዎች በጉብኝቱ ተሳትፈዋል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review