የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን በማሳካት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።
በግብርና ሚኒስቴር የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም እና የኢትዮዽያ አየር ንብረት የሚቋቋም የስንዴ እሴት ሰንሰለት ልማት ፕሮጀክት የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎችና የውሃ ሞተር ፓምፖችን ለክልሎች የማስረከብ ፕሮግራም ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ 267 የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ 1ሺህ 854 ሞተር ሳይክሎች፣ 2ሺህ 289 ፓምፖችን ለክልሎች፣ ለሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እና ለፌዴራል ፈጻሚ ተቋማት በድጋፍ አስረክበዋል ።

ድጋፎቹ በአጠቃላይ ወደ ሁለት ቢሊየን ብር ወጪ ከአጋር አካላት በተገኘ የተገዙ መሆናቸውም ተገልጿል።
በዚሁ ወቅትሚኒስትሩ እንዳሉት የግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳን ማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት ያልታረሱ መሬቶችን ወደ ምርት ማስገባት እንዲሁም በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ የማምረት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
መካናይዜሽንን ማስፋፋት፣ ፋይናንስ ተደራሽ በማድረግ የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እና የገጠሩን ኢኮኖሚ ማነቃቃት የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።