ሹም ተምቤን የተባለ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሓምሌ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ቅድመ እውቅና አግኝቶ ታኅሣሥ 5 ቀን 2018 ዓ.ም የመጀመርያ የምስረታ ጉባኤውን ማካሄዱን ገልጿል።
ፓርቲው በመስራች ጉባኤው ላይ የሹም ተምቤን የበላይ ጠባቂ ፕሬዚዳንት፣ የፓርቲውን ሊቀ መምበር፣ የማእከላዊ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚ አባላትን እንዲሁም የፓርቲውን የቦርድ አባላትና እንስፔክሽንና ቁጥጥር አባላትን የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት መምረጡን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው የበላይ ጠባቂ ፕሬዚደንት አቶ ገ/ሚካኤል ተስፋይ፣ ፓርቲው በአደራጃጀት ክልላዊ ይሁን እንጂ በአሰራሩና በፅንሰ ሀሳቡ ደረጃ ሃገራዊ መሆኑን ገልጸው፣ ከሌሎች ለዲሞክራሲ፤ለሰላምና ለልማት እንዲሁም ለሃገራዊ ጥቅም ከሚታገሉ ሀይሎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚስተዋለው ችግር በክልሉ ህዝብ የተመረጠ መንግስት ባለመኖሩ የመጣ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ገብረሚካኤል፣ ችግሩ የሚፈታውም በክልሉ ፍትሃዊና ተአማኝ ምርጫ ሲካሄድ ብቻ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
ለዚህም በትግራይ ክልል መጪው ምርጫ በተያዘለት ጊዜና የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህግጋትን ባከበረ መልኩ ተካሂዶ የመፍትሄ አካል እንዲሆን ፓርቲያቸው ሀላፊነቱን እንደሚወጣም ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ሊቀ መምበር አቶ ጎይትኦም ወልደማርያም በበኩላቸው በትግራይ ክልል ያለው የሰላም እጦትና የፖለቲካ ምህዳር መጥበብን ለመፍታት ሁሉም በየአካባቢው በመደራጀት ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲተገበር የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባዋል ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል ሰላምና ልማት እንዲሰፍን በክልሉ የሚካሄደው መጪው ምርጫ ሲተገበርና በህዝብ የተመረጠ መንግስት ሲኖር መሆኑን በመግለፅ ለዚህም ፓርቲያቸው እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በመስራች ጉባኤው ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣የአገው ተወካዮችና የተምቤን ተወላጆች ተገኝተዋል፡፡
በምሩፅ ተስፋይ