የኦንላይን ግብይትን ወደ ግብር ስርዓት ለማስገባት እየተሰራ ነው

You are currently viewing የኦንላይን ግብይትን ወደ ግብር ስርዓት ለማስገባት እየተሰራ ነው

AMN – ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ የኦንላይን ግብይትን ወደ ግብር ስርዓቱ ለማስገባት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ገለጹ።

ቢሮው ከተማው የሚያመነጨውን ገቢ በፍትኃዊነት የመሰብሰብ ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም መሆኑን የገለጹት አቶ ሰውነት፣ የሚሰበሰበውም ገቢ ለከተማዋ እድገት እና ድሕነት ቅነሳ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡

የተጀመረው የከተማዋ ልማት ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ እና የከተማዋ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ለማስቻል ቢሮው የተጣለበትን ገቢ የመሰብሰብ ተልእኮ በብቃት ለመወጣት እንዲችል የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ባለፈ የተለያዩ የገቢ መሰረቶችንም የማስፋት ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አቶ ሰውነት ተናግረዋል።

ቢሮው በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ፣ ወደ ግብር ሥርዓቱ ያልገቡ አካላትንም እየለየ ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ አመትም ከኦንላይን ግብይት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ የኦንላይን ግብይት በስፋት እየተከናወነ ከመሆኑ አንጻር እጅግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በኦንላይን ወይም በዲጂታል ማርኬቲንግ አማካይነት እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የተለያዩ የዲጂታል ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የኦንላይን ግብይት ስርዓትን ወደ ግብር ስርዓቱ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review