AMN – ታኅሣሥ 6/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለነዋሪዎች የቤት ፍላጎት እና አቅርቦትን ለማመጣጠን የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል።
ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን Cold-Formed Steel(CFS) የተባለ የግንባታ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቤቶችን የመገንባት ስራ ተጀምሯል።
ቴክኖሎጂው እስከ 12 ወለል የሚደርሱ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል።
በዓይነቱ አዲስ እና ልዩ የሆነው የግንባታ ቴክኖሎጂ የመጀመርያውን ልዩ የጋልባናይዝድ ብረት ውጤት በመጠቀም እስከ 12ወለል የሚደርሱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ባጠረ ጊዜ መገጣጠም የሚያስችል ነው ፡፡

ከአርማታ ጋር ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ የሕንፃ ከፍታቸው እስከ 23 ወለል የሚደርሱ የጋራ መኖርያ ቤቶችን በተሻለ ፍጥነት ለመገንባት የሚያስችል ነው።
ቴክኖሎጂው ቤቶችን ለዜጎች ጥራቱን በጠበቀ እና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በፍጥነት ለማቅረብ እንደሚያግዝ የተናገሩት ሀላፊዋ በግንባታው ሂደትም ለነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።
ፋብሪካውን ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ እንዳስፈላጊነቱ በአርሶ አደሩ እና በሌሎች ተገቢነት ባላቸው አከባቢዎች በመስራት የልማት ፕሮግራሙ ሁሉን ያቀፈ እና ተደራሽ ማድረግ ለዜጎች የተሻለ መጠለያ ለማጎናጸፍ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ጭምር ይጠበቃል።
አገልግሎት የጨረሱ ብረቶችን በመጠቀም የቤት ልማት ግብአቱ እንደሚመረት የተናገሩት ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገቡት የሌጋሲ ሀውሲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት ኢንጂነር ያሬድ አፈወርቅ የሚገነቡት ቤቶች ረጅም ጊዜ የሚቆዩ እና ለኢትዮጵያ አየር ንብረት ተስማሚ ናቸው ብለዋል።

ሲሚንቶ እና ሪባር ሳይጠቀሙ ብረቶችን በማጠፍ ቤቶችን እና ኮንስትራክሽን መስራት የሚያሥችለው የግንባታ ቴክኖሎጂው፤ ከወዳደቁ ብረቶች እና መሰል ግብአት የሚሰሩ በመሆኑ ቤቶቹ እንዳይዝጉ ብሎም እንዲጠነክሩ ተደርገው ስለሚዘጋጁ ሁለት እና ሶስት መቶ አመት እንደሚቆዩ አብራርተዋል፡፡
በCold-Formed Steel (CFS) ቴክኖሎጂ የሚሰሩ ቤቶቹ ለአደጋ ተጋላጭነታቸው አነስተኛ መሆኑን እና በተመጣጣኝ በዋጋም የሚቀርቡ መሆናቸው ተገልጿል ።
ቴክኖሎጂው ንፋስን እና የመሬት መንቀጥቀጥን ስለሚቋቋም በውጭ ሀገራት ተመራጭ እንደሆነ የተናገሩት ኢንጂነር ያሬድ ለእኛም ሃገር አየር ንብረት ምቹና ተመራጭ እንደሚያደርገው ገልፀው ይህም በፍተሻ የተረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል ።
ማሽኑ በሰዓት 1‚375 ሜትር በላይ እንደሚያመርት እና ይህ ደግሞ በዓመት 26 ሺህ ቤቶች በ50 ካሬ ሜትር ቦታ ሊሰራ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገራችን ከሚሰሩ ግንባታዎች አንጻር ሲታይ ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንዳለውምው ተናግረዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ