የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች የዲጂታል ዘመን ዕድልን እንዲጠቀሙበት ያስቻለው ታላቅ የስልጠና መርሐግብር ፍሬ ማፍራት ጀምሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ በቅርቡ ባስታወቀው መሠረት፣ በኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና ተማሪዎች ከንድፈ ሐሳብ አልፈው ወደ ተግባራዊ የቴክኖሎጂ ልማት ተሸጋግረዋል። ይህ ስልጠና ወጣቱን ትውልድ ለዘመኑ የዲጂታል ኢኮኖሚ እያዘጋጀው ነው።
የተገኘው አስገራሚ ውጤት ምንድነው?
ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለወጣቶች፣ ተማሪዎችና ሠራተኞች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሠረታዊ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት ሲሰጥ ለመቆየቱና የቢሮው የአቅም ግንባታና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ አምሀ ሲሳይ ምስክር ናቸው።
በተሰጠው ስልጠና በርካታ ወጣቶች ዘመኑን የዋጀ እውቀት ስላገኙ የፈጠራ ችሎታቸው ዳብሮ ትልቅ ውጤት ማስመዝገባቸውን አቶ አምሀ በማስረጃ ጭምር ነው የሚገልጹት። ለምሳሌ ያህል፦

- የኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በራሳቸው አቅም የዌብሳይት ንድፎችን (ቴምፕሌቶችን) ማዘጋጀት ችለዋል።
- የሌሎች ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ደግሞ የከተማዋን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ ልዩ ልዩ የኮምፒውተር ሲስተሞችን በማበልጸግ ላይ ይገኛሉ።
- የምገባ ፕሮግራሞች ደግሞ በቴክኖሎጂ ታግዘው በኩፖን ሲስተም መመራት መቻላቸው፣ አሠራሩን ቀልጣፋና ምቹ አድርጎታል።
- በተጨማሪም የኢትዮ ኮደርስ ማናጅመንት ሲስተም ራሱ ተገንብቷል፤ ይህም ከተለያዩ ተቋማት የሚመጡ መረጃዎች ድግግሞሽ እንዳይኖራቸው በማድረግ በአንድ ቋት እንዲሰባሰቡ ማድረግ አስችሏል።
ምን ያህል ተሳታፊዎች ተጠቃሚ ሆኑ?
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ መሆኑን ያስረዱት አቶ አምሀ ሲሳይ በመዲናዋ ከተጀመረ አንስቶ በአጠቃላይ 622 ሺህ 318 ባለሙያዎችን፣ ሠራተኞችን፣ ተማሪዎችንና ወጣቶችን አሳትፏል።
በ2018 በጀት ዓመት ላይ ያለው መረጃም አስደናቂ ነው
👉 እርሶስ ይህን የመጨረሻ ዕድል ለመጠቀም ምን አቅደዋል?
- በዚህ የበጀት ዓመት ብቻ 462 ሺህ 824 ሰዎች ተመዝግበው ሰርቲፋይ ሆነዋል ።
- ከእነዚህ ውስጥ 74.3 በመቶ የሚሆኑት ስልጠናውን ወስደው አጠናቀዋል።
- በበጀት ዓመቱ በቀሩት ወራት ደግሞ 195 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ስልጠናውን ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዕድሉን እንዳያመልጣችሁ ተጠቀሙበት!
በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ማለትም በየመሠረታዊ ፕሮግራሚንግ (Fundamental Programming)፥ የዳታ ትንተና (Data Analysis)፥ የአንድሮይድ አፕልኬሽን ልማት (Android Development) እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) ለሶስት ዓመታት ሲሰጥ የቆየው የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በተያዘው በጀት ዓመት ያበቃል። ስለዚህ አቶ አምሀ ይህ ስልጠና ከዚህ በኋላ የማይገኝ ትልቅ ዕድል በመሆኑ፣ የተመዘገቡት በቶሎ እንዲያጠናቅቁና እንዲሁም በአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ይህን ዕድል እንዲጠቀም ጥሪ አቅርበዋል። - በሔለን ተስፋዬ