ያደጉ ሀገራት ቀውስ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ በእኛ ሀገር ህግ እንዴት ይታያል?

You are currently viewing ያደጉ ሀገራት ቀውስ የሆነው ማህበራዊ ሚዲያ በእኛ ሀገር ህግ እንዴት ይታያል?

AMN- ታኅሣሥ 7/2018 ዓ.ም

ከባሕል እሴት እና ወግ ያፈነገጡ አለባበስ፣ ጸያፍ ተግባራት የሞራል እና ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የሀገራችን ህግ ምን ይላል? ሲል ኤ ኤም ኤን የህግ ባለሞያ ከሆኑት ከአቶ ኪያ ጸጋዬ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አለባበስም ሆነ ማንኛውም በቃልም ሆነ በምስል የሚገለጹ ሁነቶች የህግ ጥበቃ አላቸው ያሉት የህግ ባለሞያው፤ ማንም ሰው የፈለገውን ሀሳብ በእቅስቃሴም ሆነ በቃል በነጻነት መግለጽ የሚችል ቢሆንም፣ የወጣቶችን ጤና ለመጠበቅ እና ስነምግባር ያለው ትውልድ ለመፍጠር የራሱ የሆነ ገደብ እንዳለው አብራርተዋል።

መብት እና ግዴታ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው ያሉት አቶ ኪያ፣ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አንድ ሰው መብቱን ሲተገብር የማህበረሰቡን መብት እና ሞራል እንደማይጥስ መረጋገጥ አለበት ብለዋል።

ማህበራዊ ሚዲያን በተመለከተ አዲስ የመጣው ማህበራዊ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ለቁጥጥር የሚያስቸግር እና ድንበር ተሻጋሪ ስለሆነ፣ በተለይ ወጣቶች እና ሕጻናትን በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆኑ ቅሬታዎች እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዘርፉ ለብዙ ያደጉም ሆኑ ያላደጉ የዓለም ሀገራት ትልቅ ቀውስ ሆኗል ያሉት የህግ ባለሞያው በተለይ አውስትራልያ በቅርቡ ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎቿ ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ ኩባንያዎች ላይ ገደብ መጣሏን ገልጸዋል።

ልቅ የሆነው የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም ገደብ እንዲኖረው ብዙ ሀገራት ህጎችን እያወጡ እና እያጠበቁ መሆኑን የገለጹት የህግ ባለሞያው፣ በእኛ ሀገር ከህገ መንግስቱ ባሻገር የወንጀል ህጉ መብት እና ግዴታ የአንድ ሳቲም ሁለት ገጽታ ከመሆናቸው ባለፈ፣ አጸያፊ የሆነ ከማህበረብ እሴት እና ሞራል የተቃረነ ድርጊትን በህዝብ ፊት ያሰራጨ እና እንዲሰራጭ ያደረገ ሰው በወንጀል እንደሚጠየቅ ጠቅሰዋል።

ይህ ደግሞ የወንጀል ህግ አንቀጽ 636 ላይ በደንብ ተቀምጧል ብለዋል።

ይህ የተሻሻለው የወንጀል ህግ የዛሬ ሃያ አመት የወጣ መሆኑን በመጥቀስ፣ አዳዲስ ሁነቶችን በማየት የእኛ ሀገር ህግ አውጪዎች እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እነዚህ አጣዳፊ የሆኑ የህዝቡን ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በቂ የሆነ ህግ ማውጣት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

የወጣቶችን አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጤና መጠበቅ እንደሚገባ ይህም ትምህርት እና እውቀት ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በስነምግባር የታነጸ እና የተማረ ትውልድ ሀገር ትፈልጋለች፣ ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትምህርት ምን ያደርጋል በአቋራጭ ሀብታም ትሆናለችሁ ዞሮ ዞሮ ገንዘብ ማግኘት ነው ዋናው በማለት ትውልዱ ላይ ጫና የሚያሳድሩና ታዋቂ ለመሆን የሚደረጉ ድርጊቶች ከሞራል፣ ከስነምግባር እና ከመልካም ጸባይ የተቃረኑ መሆናቸውን በህጉ መጠቀሱን ገልጸዋል።

መንግስት እንደዚህ አይነት ተግባር የሚፈጽሙ ግለሰቦች የማጣራት፤ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በመልካም ስነምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ አለበት ብለዋል።

በማህበረቡ ውስጥ አሉታዊ መልክቶች መተላለፋቸው በጣም አደገኛ መሆናቸውን እና ሀገር ተተኪ ትውልድ እንዳይኖራት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

መንግስት ሰሞኑን በአንዳንድ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አንቂዎች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል መሆኑን እና አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል እንደሚደግፈው ተናግረዋል፡፡

ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ያለብን የተወሰኑ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚወጡ ግለሰቦችን መብት ነው ወይስ የአብዛኛው ህዝብ ጥቅምን ነው? ብለው የጠየቁት የህግ ባለሞያው በህግ ከለላ ስር ያሉ ተጠርጣሪ ወጣቶች ታርመወው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንደሚሄዱ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።

ልቅ የሆነውን የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ለማረም ከማን ምን እንደሚጠበቅ እና የመውጫ መንገዱን በተመለከተ አቶ ኪያ እንዳብራሩት፤ የህግ አውጭዎች አዳዲስ የሆኑ እነዚህን ሁነቶች ከግምት ያስገቡ ህጎችን ሊያወጡ ይገባል።

ህግ አስፈጻሚዎችም አሁን የተጀመሩት ዓይነት የህግ የማስፈጸም ስራ ይጠበቅባቸዋል።

ፍርድ ቤቶች እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ሲቀሰርቡላቸው በነጻነት በበቂ ማስረጃ በመያዝ የወንጀል ህጉን መርሆች እና የተጠርጣሪዎችን መብት ባልጣሰ መልኩ ሊያስተናግዱ ይገባል።

ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረግ አለባቸው።

በተለይ ወላጆች ልጆቻቸው ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርጉ እና ልጆቻቸውን ተከታትሎ የማረም ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ትውልድን ለመጠበቅና የዲጂታል ሥነ-ምግባርን ለማጎልበት መወሰድ ያለበት ቀጣይ እርምጃ ምን ሊሆን ይገባል? አስተያየትዎን ያካፍሉን!

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review