የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ከታኅሳስ 7-8/2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡ ይህም የሁለቱን ሀገራት የቆየ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነዉ፡፡
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በሕንድ የአፍሪካ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ ያላትን እየጨመረ የመጣውን የኢኮኖሚ ትስስር፣ የሁሉ አቀፍ ልማትና ስትራቴጂካዊ ትብብር፣ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጎላ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ዋንኛ ዲፕሎማሲያዊ ማዕከል መሆኗን ያረጋግጣል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ከተለመደው የዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ባለፈ ሕንድ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ወደዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የአለም አቀፉን የደቡብ ድምጽ በጋራ ለማጉላት ያላት ፍላጎት መጨመሩንም ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያና ሕንድ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ግንኙነት የጀመሩ ቢሆንም ሀገራቱ ከ2ሺ ዓመት በላይ የዘለቀ ጥልቅ ታሪካዊ ወደጅነት ያላቸው ሀገራት ስለመሆናቸው የተለያዩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
ህንድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በሰፊው ዓለም መካከል እንደ ድልድይ አድርጋ በማስቀመጥ በአስተዳደር፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በንግድ ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በመደገፍ ዘላቂ ወዳጅነቷን አሳድጋለች፡፡
ሕንድ ከአፍሪካ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በሰላም ማስከበር እና በዘላቂ ልማት ባሉ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለማጠናከር ፍላጎቷ ከፍተኛ ነዉ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሀገራቸዉን ቁርጠኝነትን ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል፡፡
ህንድ የኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲያድግና የጋራ ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ አጋዥ የሆነውን የብሪክስ አባል የመሆን ጥያቄ ከደገፉ አባል ሀገራት አንዷ ስትሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሻሻል በትብብር እየሰራች ትገኛለች።
ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የሚያደርጉት ዉይይትም በዋና ዋና ዘርፎች በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ኃይል ትብብር፣ በአቪዬሽን እና በዲጂታል ሽግግሮች ዙሪያ ፍሬያማ ምክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ጉብኝቱ ከሁለትዮሽ ግንኙነቶች ባለፈ ኢትዮጵያ በበርካታ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እያደገ የመጣዉን ተደማጭነቷን የሚያሳይ እና ከአለማችን 10 ግዝፉ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገራት አንዷ የሆነቸው ሕንድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጋ መቀበሏን ማሳያ ነዉ፡፡ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት