ለ50 ሺህ ሕጻናትና ቤተሰቦች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ሊካሄድ ነው

You are currently viewing ለ50 ሺህ ሕጻናትና ቤተሰቦች የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ሊካሄድ ነው

AMN – ታኅሣሥ 7/2018

የበጎ ፈቃደኛ ሴት ጋዜጠኞች፥ ደራሲያት እና ምሁራን ጥምረት ሰብሳቢ ከሜሪጆይ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታቸው ለቀሩ ከ50 ሺህ በላይ ህጻናት ዘላቂ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ልዩ የበይነ መረብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ለማካሄድ መታቀዱን የጥምረቱ ሰብሳቢ ጋዜጠኛ ሮማን ተገኝ ገልጸዋል፡፡

ከጥር 20 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የተገለጸው የገቢ ማሰባሰቢያ በተለያዩ ምክያቶች ለከፋ ችግር የተጋለጡ ሕፃናት ወደትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ “የእኔም ልጆች ናቸው”በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ነው በመግለጫው የተገለጸው።

እስከዛሬ ድረስ ችግሩን ለመፍታትና ሕፃናቱ የተለያዩ ዕድሎችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ በተለያየ መልኩ ድጋፍ ሲያደርጉ ለቆዩ ከግለሰብ እስከ ተቋማት ድረስ ላሉት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሆኖም ግን ተጋላጭነቱ አሁንም በሚስተዋልባቸው አምስት የሀገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ ሕፃናት መድረስ ስለሚያስፈልግ ይህ መርሐ ግብር መዘጋጀቱን የጥምረቱ ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን›› በሚል ላለፉት 22 ዓመታት ከ8 ሽህ በላይ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን በመደገፍ እራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ የሚገኘው የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴም በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩን በመደገፍ ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለመርዳት በንቅናቄው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዝናሽ ሞዲ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review