ከምክክር ሂደቱ ራሳቸውን ያገለሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖችን ወደ ምክክሩ ማምጣት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዋና ፀሐፊው የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ግዋንግ ኮንግ ጋር በፅሕፈት ቤቱ ተወያይቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰላም ግንባታ ሂደቶች ላይ በምስራቅ አፍሪካ በርካታ ተግባራት እንደሚያከናውን ኮሚሽኑ አስታውሶ በኢትዮጵያ የሚደረጉ የሰላም ግንባታ ሂደቶች ላይ ድርጅቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በእስካሁኑ የምክክር ሂደት ራሳቸውን ያገለሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች እና ታጣቂ ቡድኖች መኖራቸውን ጠቁሞ እነዚህን አካላት ወደ ምክክር በማምጣቱ ረገድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሊደረግለት ስለሚገባው ልዩ ልዩ ድጋፎች ገንቢ ውይይት ማድረጋቸዉን ኮሚሽኑ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡