AMN – ታኅሣሥ 8/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የስልጣኔ ታሪክ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪኮች ዛሬ ላይም በተራሮች፣ በሸለቆዎች እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ይህ የስልጣኔ ውጤት እና ጥበብ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለምታደርገው አውነተኛ የብልፅግና ጉዞና ለቀጣዩ ዘመን ስኬት እንደሚያነሳሳ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያንና ህንድን የሚያመሳስሏቸው በርካታ የስልጣኔ ታሪኮች መኖራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነትም በኢትዮጵያ ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የተሰሩትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና በተመሣሣይ በህንድም ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተሰሩ ሀውልቶችን አንስተዋል፡፡

እነዚህ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ሁለቱ ሀገራት የነበራቸውን የዕድገት ደረጃና የእርስ በርስ ግንኙነት ማሳያ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ላይም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የቆየ ግንኙነት አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ እንደሆነች ሉሲን በአብነት የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ሁላችም የመጀመሪያው የዘር ሀረጋችን አንድ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ህንድ ከ2 ሺህ አመታት በላይ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውንና የቆየ የንግድ ትስስር እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ዜጎች በንግድ ሲገናኙ ስለሚገዟቸውና ሚሸጧቸው ሸቀጦች ብቻ ሳይሆን የሚያተኩሩት ሀሳብና ታሪክ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤዎችን ልምድ ይለዋወጡ ነበር ብለዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የህንድ መምህራን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እውቀትና ክህሎታቸውን ለኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ያካፍሉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ዛሬ ላይም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁን ወቅት በግብርና፣ በኢንቨስትመንት፣ በወታደራዊና በሌሎች ዘርፎችም የሚደረገው ትብብሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን