የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት ክርስቲያን ተራድኦ ኮሚሽን በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ለ6 ወረዳ ነዋሪዎች ስምንት ሚልዮን ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የቁሳቁስ ድጋፉ የተደረገው በኮሚሽኑ ስር ባለው ምኞቴ ፕሮጀክት በኩል ሲሆን፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የተፈናቀሉ የሀገር ውስጥ ዜጎች፣ የውጭ ሀገር ስደተኞች እና ተቀባይ ማህበረሰቦች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
የተደረገው ድጋፍ ‘ራስ ማስቻል እና ከድህነት ማውጣት’ የሚል አላማ ያለው ስለመሆኑም ተገልጿል።

ድጋፉ ስደተኞች እና ተቀባይ ማህበረሰቡ በጋራ በሚገለገሉባቸው እንደ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፣ የወንበር፣ የኮምፒውተር እና አጋዥ መጽሐፍትን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያካተተ ነው።
በስደተኞችና በስደተኛ ተቀባዩ ማህበረሰብ በኩል ያለው መስተጋብር እንዲጠናከር መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማት ክርስቲያን ተራድኦ ኮሚሽን፤ አሁን ላይ በምኞቴ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ለ5 መቶ ቤተሰቦች ቀጥተኛ ወርሀዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ ስለመሆኑ ገልጿል።
በቶማስ አሊጋዝ