በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ከ300 መቶ በላይ የሺሻ ማስጠቀሚያ እቃዎችና በርካታ አደንዛዥ ዕፆች መወገዳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም 171 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ተገልጿል።
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከክፍለ ከተማው አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት፤ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ቤት እና የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በክፍለ ከተማው ስር በሚገኙ 11 ወረዳዎች የኦፕሬሽን ስራ መከናወኑ ተገልጿል።
በዚህ የኦኘሬሽን ስራ የተሰበሰቡ 3 መቶ 76 የሺሻ ማስጠቀሚያ እቃዎች፣ ከ11 ኪሎ ግራም በላይ ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ ዕፅና የምግብ እጥረት ላለባቸው ህፃናት የሚሰጥ በኮንትሮባንድ ባንድ መልኩ የገባ 175 እሽግ ፕላም ፕሌት እንዲሁም የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎች ላይ የሚገጠም 107 እሽግ ፒፓ መወገዱን የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዲቪዚዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር ተዘራ ከፍያለው ተናግረዋል።

ጊዜው የትምህርት ወቅት በመሆኑ ፖሊስ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ለወንጀል መከላከልና ለመማር ማስተማሩ ሂደት እንቅፋት የሚሆኑ አዋኪ ድርጊቶችን ለማስወገድ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ኢንስፔክተር ተዘራ ጠቅሰዋል።
ሺሻ መጠቀምም ሆነ ማስጠቀም የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንዳይኖር፤ ወጣቱ አልባሌ ቦታ እንዲውል የሚያደርግ ጎጂ ተግባር በመሆኑ በተለይ ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦች ለማንና ለምን ተግባር ማከናወኛ እንደሚውል መቆጣጠር አለባቸው ሲሉ ኃላፊው አሳስበዋል።
የክፍለ ከተማው አስተዳደር ሠላምና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ቢሉ በበኩላቸው ፣እነዚህ የሺሻ ማስጠቀሚያ ዕቃዎችና አደንዛዥ ዕፆች የክፍለ ከተማውን ሠላምና ደህንነት በማወክ ወጣቱ በሱስ እንዲጠመድና በተለያየ የወንጀል ተግባር ላይ እንዲሳተፍ የሚገፋፋ ጎጂ ተግባር በመሆኑ በፖሊስና በሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም በህብረተሰቡ ትብብር ተሰብስበው መወገዳቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም የወጣቱን የስራ አጥ ቁጥር በመቀነስ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠሩ በኩል የክፍለ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም የወንጀል መንስኤ በሚሆኑ ነገሮች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰዱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 አንቀፅ 49 ንዑስ ቁጥር 5 እና አንቀፅ 67 ንዑስ ቁጥር 23 ላይ ማንኛውም ሰው የሺሻ ምርትንም ሆነ ሌሎች የተከለከሉ ምርቶችን ያመረተ፤ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከፋፈለ፣ያከማቸና በችርቻሮ የሸጠ ወይም ያስጠቀመ እንደሆነ ከ3 ወር እስከ 3 አመት በሚደርስ እስራትና ከብር 1ሺህ እስከ 2 መቶ ሺህ ብር እንደሚቀጣ ይደነግጋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሺሻ ሲያስጠቅሙና ሲጠቀሙ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅ ይዘው የተገኙ 171 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑም ተገልጿል።
ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የተወገደው የሺሻ ማስጠቀሚያ ዕቃና አደንዛዥ ዕፅ ብዙ ወጣቶችን ከጉዳት የታደገና ለከተማዋ ሠላም መረጋገጥ ማሳያ በመሆኑ ይህንን ተግባር በመደገፍና ወጣቱን በማስተማር ከፀጥታ ኃይሉ ጎን እንደሚሰለፉ መናገራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል ፡፡