የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተዉ ዘግበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የሁለቱን ሃገራት ታሪካዊ ወዳጅነት ያጠናክራል የተባለለትን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ መግባታቸዉን መገናኛ ብዙኃኑ በስፋት ዘግበዋል፡፡
አናዶሉ፥ ኢንዲያን ኒዉስ፥ አፍሪካን ኒዉስ፥ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ፥ ዘ ሒንዱ፥ አሶሼትድ ፕሬስ፥ ሬዉተርስ፥ አልጀዚራ እና ኦል አፍሪካን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ናሬንድራ ሞዲ በአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን በፊት ገጻቸውና በአርዕስተ ዜና ይዘዉ ወጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕንድ አቻቸው “የኢትዮጵያን የክብር ኒሻን” መሸለማቸዉ ደግሞ በአብዛሃኛዎቹ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ያገኘ መረጃ ሆኗል፡፡
ኢንዲያን ኒውስ ለናሬንድራ ሞዲ የተሰጣቸውውን ይህንን የኒሻን ሽልማት በሰበር ዜና ይዞት ወጥቷል።
ሽልማቱ 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ላላት ሕንድ የተሰጠ የክብር ሽልማት ነው ሲል ዘግቧል፡፡
የክብር ኒሻኑ ለሀገርና ለህዝብ የላቀ ስራ ላበረከቱ፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ ወይም በማህበራዊ ዘርፎች ችግሮችን መፍታት ለቻሉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ድርጅቶች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ልዩ ድጋፍ ላደረገ ሀገር ወይም መሪ የሚሰጥ ነዉ፡፡
ቢል ጌትስ የዚህ ሽልማት የመጀመሪያው እና ብቸኛው ተሸላሚ ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ይህንን ሽልማት የተቀበሉ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሀገር መሪ ሆነዋል ሲል ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የአድዋ ድል መታሰቢያን መጎብኘታቸዉን፥ በኢትዮጵያ ፓርላማ ተገኝዉ ንግግር ማድረጋቸዉን፥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸዉን መገናኛ ብዙኃኑ ተቀባብለዉ ዘግበዋል፡፡

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገፆች ከፍተኛ ተከታይ ያላቸዉ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በግል ማህበራዊ የትስስር ገጻቸዉ ጭምር ጉብኝታቸዉን በቢሊዮን ለሚቆጠር ለዓለም ሕዝብ አጋርተዋል፡፡
በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ተመሳሳይ መረጃ ያጋሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕንድ አቻቸው በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የጋራ ዕድገትን ለመተለም አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊ እጥፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግስት ላደረገላቸዉ የክብር አቀባበል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ