ሕንድ በዓለም ላይ በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ እና ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸዉ ሃገራት መካከል አንዷ ናት።
በጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) መጠን ከዓለም በ5ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ በግዢ አቅም ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዛለች። ሕንድ ከኢኮኖሚዉ በዘለለ በፖለቲካ፣ በወታደራዊ አቅም፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና መሰል መስኮች ትታወቃለች፡፡
በፊልም ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ሃገራት መካከልም ሕንድ ዋንኛዋ ነች፡፡ የሕንድ ፊልም ኢንዱስትሪ ወይም የሕንድ ሲኒማ በዓለም ላይ በፊልም ብዛትና በተመልካች ቁጥር ቀዳሚው ነው። የሕንድ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ከአንድ ቋንቋ በላይ ያላቸዉ የተለያዩ ክልሎች የፊልም ኢንዱስትሪዎች ስብስብ ነው።
በሕንድ በዓመት በአማካይ ከ1 ሺህ 500 እስከ 2 ሺህ ፊልሞች ከ20 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች እንደሚዘጋጁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በሕንድ ከሚገኙ ዋና ዋና የፊልም ማዕከላት እና ፊልሞች በተለያዩ ቋንቋቸው ከሚዘጋጁባቸው ቦታዎች መካከል ቦሊዉድ፣ ቶሊዉድ፣ ኮሊዉድ እና ሞሊዉድ የሚባሉት ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡
ቦሊዉድ በሙምባይ የሚገኝና በሂንዲ ቋንቋ ፊልሞችን የሚያመርት ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም የሚታወቅ የሕንድ ፊልም ክፍል ነው። በቴሉጉ፤ በታሚል እና በማላያላም ቋንቋዎች የሚመረቱ ሲኒማዎችም ተከታዩን ደረጃ ይይዛሉ፡፡
በሕንድ የሲኒማ ኢንዱስትሪ ዉስጥ እ.ኤ.አ ከ1940ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ያሉት ዓመታት የሕንድ ሲኒማ ወርቃማ ዘመን ተብለዉ ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ወቅት ላይ ማዘር ኢንዲያን “Mother India” የመሰሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ፊልሞች ተሠርተዋል።
የሕንድ ፊልሞች በአብዛኛዉ በፍቅር፣ በድርጊት (Action)፣ በኮሜዲ እና በሙዚቃ ድብልቅ ይታወቃሉ፡፡ ዘፈን እና ዳንስ የሕንድ ፊልሞች ዋነኛ አካልና መለያዎች ናቸው።
የሕንድ ፊልሞች በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነት አላቸው። በተለይም በ90ዎቹ እና በ2000ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሕንድ ፊልሞች በቪዲዮ ቤቶችና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በስፋት ይታዩ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ብዙ የሕንድ ፊልሞች በአማርኛ ተተርጉመው ለተመልካች እየቀረቡ ይገኛሉ።
ለመሆኑ ከሕንድ ፊልሞች በየትኞቹ ተማረኩ? ያጋሩን !
በወንድማገኝ አሰፋ