የኢፌዴሪ አየር ሃይል በ2030 ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ሃይል ለመሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing የኢፌዴሪ አየር ሃይል በ2030 ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ሃይል ለመሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑ ተገለጸ

AMN ታኅሣሥ 9/2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ አየር ሃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አደዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።

በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር አየር ሃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከወራሪ ጠብቆ የቆየ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጊዜያት ከህዝብ ጎን በመሆን ወገንተኝነቱን በተጨባጭ ያሳየ ጭምር ነው ብለዋል።

የአየር ኃይሉ የ90 ዓመታት የድል ታሪክ ብቻ ሳይሆን የካበተ የተቋም ግንባታ ታሪክና ልምድ ጭምር ያለው ሕዝባዊ ተቋም ነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ሲያካሂዳቸው የነበሩ የሪፎርም ስራዎች ሠራዊቱንና ሎጂስቲክሱን ብቻ ሳይሆን ግቢውንና የስልጠና ፋሲሊቲዎችን ጭምር በውስጥ ሃይል በማዘመን ሞዴል ያደረገበት ሂደት አስገራሚ ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ለድርድር በማይቀርብ ደረጃ ለማስከበር በሰው ኃይል እራሱን እያበቃ፣ በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ፣ በአየር መከላከል እና የውጊያ መሰረተ ልማቶችን ዘመኑ በደረሰበት ደረጃ በማድረስ፤ በቀጠናው ቁጥር አንድ መሆን ችሏልም ብለዋል።

የዘመኑን ቴክኖሎጂ መሸከም የሚችሉ ሙያተኞችን በስልጠና በማፍራት ፣ ሌሎች ሎጂስቲክሶችን በራስ አቅም በማምረትና በመጠገን ፣ ለሀገራችን የኢንዱስትሪ ዕድገት ጭምር ታሪካዊ አሻራውን እያኖረ ያለ የሀገር ሀብት የሆነ ተቋም ጭምር መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ የኢፌዴሪ አየር ሃይል በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ እድሜ ጠገብ ተቋማት ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልጸው በእነዚህ ዓመታት በተለያዩ ውጣውረዶች ውስጥ አልፏል ብለዋል።

ተቋሙን በ2030 ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ሃይል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል አዛዡ የ90ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ተቋሙን ለመዘከር እና ከሪፎርሙ ወዲህ የደረሰበትን ደረጃ ለዜጎች አና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ ደርሶ የኢትዮጵያ ነጻነት እና ሉዓላዊነት አስከብሯል ያሉት ሜጀር ጀነራል ነገራ አየር ሃይሉ በሰው ሃይል ስልጠና ፣ በትጥቅ እና በሁሉም የአየር ሃይሉ መገኛዎች የተለያዩ ልማቶች ማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review