የኢትዮጵያና የሕንድ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለተቀረው ዓለም ጥልቅ መልዕክት የተላለፈበት መሆኑ የሰላምና ደህንነት ተመራማሪው ገልፀዋል።
ተመራማሪው ሙሉጌታ አየነ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ የተደረገላቸው የክብር አቀባበልና በ2ቱ ምክር ቤቶች ፊት ያደረጉት ንግግር የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነት አዲስ ምዕራፍ ያመላከተም ብቻ ሳይሆን ከፍታ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ብለዋል።
የሀገራቱ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት እያደገ መምጣት ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ፣ ፍላጐቷንና ከፍታዋን ለዓለም የምታሣይበት መሆኑን የሠላምና ደህንነት ተመራማሪው ገልፀዋል፡፡
የሀገራቱ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነትና ሁለገብ ትብብር፦ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፖለቲካ፣ ትምህርት፣ ወታደራዊ እና ባህል ዘርፎች ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ሀገራቱ በጥንታዊ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት በአክሱም ዘመን መንግስት የንግድ ልውውጥ የጀመረ ጥልቅ ታሪክ ያላቸው ናቸው።
አሁን ላይ ሕንድ በኢትዮጵያ የ5 ቢሊዮን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ እና ለ75 ሺህ ዜጎች ስራ በመፍጠር ቀዳሚ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ በዚህም የሁለቱ ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር ጠንካራ መሆኑን ያሳያልም ብለዋል።
ሕንድና ኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ ሀገራት መሆናቸው እንደሚያመሳስላቸው ተመራማሪው ገልፀው፤ በኢትዮጵያ ያለው ብዝሀነት፣ ባህል፣ ወግና ልማድ በተመሣሣይ መልኩ በሕንድም እንደሚፀባረቅ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ እና ሕንድ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ለማጠናከር በርካታ የትብብር ማዕቀፎች እና ስምምነቶች መፈራረማቸውንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ከአክሱም ዘመን መንግሥት ጀምሮ ሕንዳውያን ነጋዴዎች በቀይ ባሕር እና በህንድ ውቄያኖስ በሚገኙ ወደቦች አማካኝነት የንግድ ልውውጥ ያደርጉ እንደነበር አስታውሰዋል።
በ1948 ዓ.ም በይፋ የጀመረው የሀገራቱ ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት ሁሉን ዓቀፍ የትብብር መድረክ ላይ መድረሱን ሙሉጌታ አየነ (ዶ/ር) አብራርተዋል።
በበረከት ጌታቸው