ጋናዊቷ የሕዝብ እንደራሴ የተደመሙበት የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት

You are currently viewing ጋናዊቷ የሕዝብ እንደራሴ የተደመሙበት የአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት

AMN-ታኅሳስ 9/2018 ዓ.ም

3ኛዋ የዓለም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል፤ የፓን አፍሪካ ትርክት እምብርት፤ የአሕጉሪቱ ፖለቲካ አስኳል እና የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ በመሆኗ በበርካቶች እየተጎበኘች ትገኛለች አዲስ አበባ ከተማ።

ሰሞኑን የጋና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሃጂያ ዙወራ መሀመድ በሥራ ጉዳይ አዲስ አበባ ቆይተው ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ፤ ለጋና ፓርላማ አባላት ስለ አዲስ አበባ የተናገሩት በመገናኛ ብዙኋን እየተዘገበ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ደግሞ በስፋት እየተዘዋወረ ይገኛል።

“በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ካረፍኩበት ሆቴል ወደ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በመኪና እየተጓዝኩ አዲስ አበባ ከተማ እጅግ አስገራሚ ዕድገት እያስመዘገበች መሆኗን ማየት ችያለሁ” ብለዋል ሃጂያ ዙወራ መሀመድ።

“በጉዟችን ወቅት አዲስ አበባ እያስመዘገበችው ስለላው አስደማሚ ዕድገት ብቻ ነበር ስናወራ የነበረው” በማለት ነው ለፓርላማው የአዲስ አበባን ዕድገት የገለጹት።

የአዲስ አበባን ዕድገት እና ለውጥ “እኛ ጋናውያንስ በሀገራችን ምን ሰራን? ይህን መሰል ልማት በአዲስ አበባ እንዴት ሊሰካ ቻለ?” ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅ ያደረገ ነውም ብለዋል።

“ከ5 ዓመታት በፊት የማውቃትን አዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ ሄጄ ስመለከታት መለየት እስኪቸግረኝ ተለውጣ፤ እጅግ ዘመናዊ ሕንፃዎች ተገንብተው፤ ባለ 4 እና 5 መስመር ያላቸው የመኪና መንገዶች ተሰርተው አይቻለሁም” ነው ያሉት።

በከተማዋ ለእግረኞች እና ለብስክሌት ተጠቃሚዎች የተሰሩ መንገዶችም እጅግ ሰፊና ዘመናዊ መሆናቸውንም እንደታዘቡ የሕዝብ እንደራሴዋ ለም/ቤቱ አብራርተዋል።

በከተማው መንገድ ዳሮች ያለው ክፍት፣ ንጹሕና ፅዱ የአረንጓዴ ስፍራ ለኢትዮጵያውያን አረፍ የሚሉበት እና የሚዝናኑበት አማራጭ የፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።

የጋና ምክር ቤት አባልዋ ሃጂያ ዙወራ መሀመድ “እኛ ጋናውያን ከተሞችን በማዘመን ለዜጎችና ለቱሪስቶች ምቹ ማድረግን ከኢትዮጵያ ልንማር ይገባል” በማለት ለምክር ቤቱ አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review