’’ዝምተኛው ገዳይ’’ ኮሌስትሮል

You are currently viewing ’’ዝምተኛው ገዳይ’’ ኮሌስትሮል
  • Post category:ጤና

AMN – ታኀሣሥ 10/2018 ዓ/ም

ኮሌስትሮል በደም ውስጥ የሚገኝ ስብ መሰል ንጥረ ነገር ሲሆን፣ ለሰውነት ከሚያስፈልገው መጠን በላይ ሲበዛ የደም ስሮችን በማጥበብ ለልብ ድካምና ለድንገተኛ ስትሮክ (Stroke) ይዳርጋል።

ኮሌስትሮል ለነርቭ፣ ለደም ስርና አጠቃላይ ለሰውነት ክፍሎች ከፍተኛ ጠቀሚታ ያለው ንጥረ ነገር ሲሆን፤ 7ዐ በመቶ የሚሆነው በጉበት አማካኝነት ከሰውነት እንዲሁም 3ዐ በመቶ ከምንመገበው ምግብ ይመረታል፡፡

ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን በአብዛኛው ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዘ መሆኑን በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጂ የሥነ ምግብ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ከበቡሽ አለሙ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ በተለይ ስብ የበዛባቸው ምግቦች፣ ቅቤ፣ ስጋ እና በዘይት የተጠበሱ ምግቦች መመገብ እንዲሁም አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ የኮሌስትሮል መጠንን ይጨምራሉ።

ሲጋራ ማጨስና አልኮል መጠጣት፣ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት እንዲሁም በዘር (Genetics) ከቤተሰብ መካከል በበሽታው የተጠቃ ሰው ካለ ለአላስፈላጊ የኮሊስትሮል መጠን መጨመር መንስኤ መሆኑን ወ/ሮ ከበቡሽ አብራርተዋል፡፡

በአላስፈላጊ የኮሊስትሮል መጠን መጨመር የሚከሰተውን የጤና ችግር የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር ብቻ መከላከል ይቻላል፡፡

በተለይ ፋይበር (Fiber) ያላቸውን ምግቦች እንደ አጃ (Oats)፣ ባቄላ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ከቅባት እህል ለውዝ፣ ሰሊጥ እና የወይራ ዘይትን መጠቀም የተስተካከለ የኮሊስትሮል መጠን በሰውነት ውስጥ እንዲኖር ይረዳል፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር እና በቂ እረፍት ማግኘት አላስፈላጊ የኮሊስትሮል መጠን መጨመርን መከላከል ያስችላል።

መጠኑ በጣም ከፍተኛ የሆነ ኮሊስትሮል በሰውነት ውስጥ መኖሩ ከተረጋገጠ የኮሌስትሮል መጠንን የሚቀንሱ መድሃኒትችን በሀኪም ትዕዛዝ በመውሰድ ማከም ይቻላል።

የኮሌስትሮል መጠን መጨመር ምልክት ላያሳይ ስለሚችል፣ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ምርመራ በማድረግ አላስፈላጊ የኮሊስትሮል መጠን መጨመርን እና በሱ ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻል ወ/ሮ ከበቡሽ አለሙ ገልፀዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review