የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ። ይህ የተገለጸው የኑሮ ውድነት እና የገበያ ማረጋጋት ግብረ-ኃይል ባለፉት አምስት ወራት ያከናወናቸውን ሥራዎች በገመገመበት ወቅት ነው።
በግምገማው ወቅት በሰብል፣ በፍራፍሬና በአትክልት አቅርቦት ረገድ የተሻሉ ውጤቶች ቢመዘገቡም፣ አሁንም የኅብረተሰቡን እርካታ በሚገባ ማረጋገጥ ባለመቻሉ በቀጣይ ወራት የዋጋ ንረትን ማረጋጋት የከተማ አስተዳደሩ ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

የምርት አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሳደግ በከተማ ግብርና እና በሌማት ትሩፋት የሚሠሩ ሥራዎችን ከማጠናከር ባለፈ፣ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ የምርት መጠን ወደ ከተማዋ እንዲገባ የማድረግ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳጠርና ደላሎችን ለማስቀረት የሸማች ማኅበራትንና የንግድ ድርጅቶችን አቅም መገንባት፣ የሰንበት ገበያዎችን ጥራት ማስጠበቅ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርቡ ማድረግ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው።
በነጻ ገበያ ስም ምርት በመከዘንና ጊዜን ጠብቆ ካለአግባብ ዋጋ በመጨመር ገበያው እንዳይረጋጋ በሚያደርጉ አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እንደሚደረግ ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል።
ለዚህ ተግባር ስኬታማነት በየደረጃው ያለው አመራር በቁርጠኝነት እንዲሠራ የተጠየቀ ሲሆን፣ የመድረኩ ተሳታፊዎችም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ በማድረግ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በሔኖክ ዘነበ