ከ60 ሚሊየን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ወርቅና ከ4ሚሊየን ብር በላይ ይዘው በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እንደገለጸው ተጠርጣሪዎቹ በአሶሳ ከተማ አምባ አንድ በሚባል ቦታ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከነኤግዚቢቱ ነው፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረው ወርቁና ጥሬ ገንዘብ ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ሊውል የቻለው ምምሪው ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ባደረገው ክትትል መሆኑን በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ፥ የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ፖሊስ፥ ሬጅመንት አንድ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዳኜ ዓለማየሁ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ገልጸው የተያዘው ወርቅና ጥሬ ገንዘብም ለአሶሳ ከተማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮንትሮባንድና ሕገ-ወጥ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ እና በሕጋዊ ነጋዴዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመገንዘብ ከሕዝብና ከመንግሰት የተጣለበትን አደራ ለመወጣት ሕዝብን ባሳተፈ መልኩ ስኬታማ የመከላከል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ፌደራል ፖሊስ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡