የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ፎረም የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ሥራን በስትራቴጂካዊ መንገድ በመሥራት ለሀገር ግንባታ የተቀመጡ ግቦችን እያሳካ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ፡፡
የሚዲያ እና የሕዝብ ግንኙነት ፎረም የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን መሠረት የማስያዝ፣ የብሔርተኝነት እና የኢትዮጵያዊነትን ሚዛን የመጠበቅ እንዲሁም የሐሰት መረናችን የመከላከል ዋና ዋና አጀንዳዎችን በማንገብ ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።
ፎረሙ ባለፉት አራት ዓመታት በኮሙኒኬሽንና በሚዲያ ሥራዎች ላይ በጋራ ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ የ2018 ዓ.ም የባለፉት አምስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በአዳማ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋን ጨምሮ ሌሎች የፎረሙ አባላት ተሳትፈዋል፡፡

የፎረሙ ሰብሳቢ እና የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ፤ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ሥራዎችን ግብ ለማድረስ ተደራጅቶ መሥራትና በአጀንዳ ቀድሞ መገኘት በዚህ ድኅረ ዓለም ውስጥ ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን እውነት በመገንዘብ የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ሥራ በስትራቴጂካዊ መንገድ፣ በእቅድ የታገዘና በአጀንዳ የሚመራ ሆኖ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ በዚህም ትልልቅ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል።
መንግሥት የድህነትና የኋላ ቀርነት አዙሪትን በመስበር የበለጸገችና ብዝሃነት የሚከበርባትን ሀገር ለመገንባት በጀመረው የብልጽግና ጉዞ ድሎች እየተመዘገቡ መሆኑን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል።
የፎረሙ ሚዲያዎችም ከጥቃቅን ኩነቶች ወጥተው በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሠሩት ሥራ ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል የሚዲያ ቅንጅትን በማጠናከር በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ በትኩረት መሠራቱ መረጃን ለመምራትና በአጀንዳ ቀድሞ ለመገኘት ማስቻሉንም ጠቁመዋል።
በዚህም በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ የሚፈጠሩ ብዥታዎችን በማጥራትና ግልጽነትን በመፍጠር ሕዝቡን ለታላላቅ ግቦች ማሰለፍ መቻሉን የገለጹት አቶ ኃይሉ፣ ድሎችን የማጽናትና የሕዝብ አንድነትን የማጠናከር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸዉን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡