ከመዲናዋ እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ነው

You are currently viewing ከመዲናዋ እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ነው

AMN – ታኅሣሥ 10/2018 ዓ.ም

ከመዲናዋ እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን የአዲስ አበባ ዋና ሥራ አስኪያጂ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ከተማዋ በፍጥነት እያደገች መሆኗን ገልጸው ከንግድና አገልግሎት ፍላጐት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት ወቅቱ የሚጠይቀውን አሰራር መከተል ይገባል ብለዋል፡፡

ለዚህም ሰዎች አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋም ሳይመጡ ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ በወረቀት ላይ የተመሠረተውን አሰራር ወደ ዲጂታል ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በስማርት ሲቲ ኢኒሸቲቭ የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ባለፉት 3 ዓመታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ኢንጂነር ወንድሙ አብራርተዋል፡፡

እስካሁን የፋይዳ መታወቂያን ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ሥራ በአጠቃላይ ከ7 ሚሊዮን 2 መቶ 6ዐ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡

ለከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለንግድ እንቅስቃሴ ከሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ዜጎችም ዲጂታል መታወቂያ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የመንግስት አገልግሎቶችን ከወረቀት ሥራ ወደ ዲጂታል ለመቀየር በጀመረው ተግባር የሲቪል ምዝገባና የዜጎች አገልግሎት የአሰራር ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፋይዳ መታወቂያ ከመንግስት አገልግሎቶች ጋር የማሰተሳሰር ሥራም እየተሰራ ሲሆን፤ የትምህርት ቤት ምዝገባ ላይ አስገዳጅ እንዲሆን በማድረግ ባለፈው ዓመት ከ850 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዲጂታል እንዲመዘገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሠረትም ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት አካውንቶቻቸውን ከዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲያስተሳስሩ መጠየቃቸውንና ይህም ሁለት ማንነት ይዞ የሚንቀሳቀስ ሰውን በመለየት ወንጀልን ለመካላከል እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

የፋይዳ መታወቂያ መውሰድ በራሱ አስገዳጅ ባይሆንም አገልግሎት ለማግኘት ግን አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን ዋና ስራ አስኪያጁ ኢንጂነር ወንድሙ አስገንዝበዋል።

ይህም ከውልደት እስከ ሞት ድረስ ማንነቱ የሚታወቅ ዜጋ ለመፍጠር የስማርት አዲስ አበባ እና የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ ለማሳካት ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review