መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እንደ ሀገር ትኩረት ለሰጠው የዲጂታላይዜሽን ልማት ጉዞ ጉልህ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማዕከል ደረጃ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት፤ ተደራሽነቱን በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡም በቦሌ ክፍለ ከተማ ተጨማሪ ቅርንጫፍ በመክፈት ሥራውን ጀምሯል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን የዚህን ማዕከል አሁናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ እና እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ቃኝቷል፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የቦሌ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት ሚሊዮን ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፤ “ክፍለ ከተማው በአጠቃላይ ተግባራት አፈጻጸም ከአሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ቀዳሚ ለመሆን ችሏል፡፡ ካስመዘገበው ስኬት በተጨማሪ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በይፋ ማስጀመር መቻሉ ለተጨማሪ ድል እገዛ ያደርግለታል” ብለዋል፡፡
እንደ ስራ አስኪያጇ ገለፃ፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራውን ከጀመረ ሁለት ወር ሆኖታል፡፡ ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ በመስጠት እና ምቹና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የተገልጋዩን እንግልት መቀነስ አስችሏል፡፡
አገልግሎቱ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ስራዎችን የሚያስቀር መላ ከመሆኑ ባሻገር በመንግስትና ህዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር የሚያደርግ የዘመነ የአሰራር ስርዓት መሆኑንም ስራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡
ተገልጋዮች ምን ይላሉ?
ወጣት ሞቲ ብርሃኑ ይባላል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ነዋሪ ነው፡፡ የልደት ምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬ) ላይ የጀርባ ማህተብ ለማስመታት እንዲሁም የነዋሪነት መታወቂያው የቆይታ ጊዜው ስላለቀ ለማሳደስ ነው ወደ ማዕከሉ የመጣው፡፡ “ብዙ ጊዜ ሳይወስድብኝ፣ ወደተለያዩ ተቋማት ሳልንቀሳቀስ አገልግሎቱን በማግኘቴ ተደስቻለሁ” ሲል ገልጾልናል፡፡
“ከዚህ ቀደም መታወቂያ ለማውጣት እና ለማሳደስ ሌሊት መጥቼ ወረፋ እጠብቅ ነበር፡፡ ‘ሲስተም የለም፤ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ናቸው ጠብቅ’ የሚሉ የተለመዱ የሚመስሉ ምላሾችን ከአገልጋይ ተቋማት ሠራተኞች በተደጋጋሚ መስማቱ ምን ያክል የተቋማት ያልዘመነ አሠራር ተገልጋይን ለምሬት ዳርጎ እንደቆየ የሚያሳይ ነው፡፡” የሚለው ወጣት ሞቲ፣ አሁን ግን በተቻለ ፍጥነት በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ጉዳዩን ከአምስት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉንና በተደረገው ለውጥ መደነቁን አብራርቷል፡፡
ቀድሞ ከነበረው አሠራር በእጅጉ የተሻለ ፍጥነትና ጥምረት የታከለበት አገልግሎት ለማግኘት ስለመቻላቸው የሚናገሩት ደግሞ በክፍለ ከተማው ወረዳ 2 ነዋሪ የሆኑት አቶ ታፈሰ ወንድማገኝ ናቸው፡፡ የመጡበት ጉዳይ በአንድ መሶብ አገልግሎት ውስጥ ከሚሰጡት አገልግሎቶች አንዱ በሆነው የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን አገልግሎትን ለማግኘት ነው። በአንድ አጋጣሚ መኪና ገጭቷቸው አምልጦ የነበረን አሽከርካሪ በያዙት መረጃ አማካኝነት ማንነቱ እንዲታወቅላቸውና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድላቸው ላቀረቡት ጥያቄ፤ በማዕከሉ ወዲያው የአደጋ አድራሹን አድራሻ በአጠረ ጊዜ ውስጥ እንዳገኙላቸው አስረድተዋል፡፡
አቶ ታፈሰ ጉዳያቸውን ወደ አንድ ማዕከሉ ይዘው ሲመጡ ወረፋ ይበዛ ይሆን የሚል ስጋት እንደነበራቸው ነግረውናል፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከ5 ደቂቃ ባጠረ ጊዜ ውስጥ መገልገላቸውን ሲናገሩ ከፊታቸው ላይ ደስታ ይነበብባቸው ነበር፡፡ ከዚህ ቀድም በነበረው አገልግሎት አሰጣጥ ከአንዱ ቢሮ ወደ ሌላው ይንገላቱና ቀናቸውን እንደዋዛ ያሳልፉ ነበር፡፡ የቀጠሮ ቀን ከመብዛቱ ባሻገር በስራ ገበታቸው ላይ በአግባቡ እንዳይገኙ ጭምር ያደርጋቸው እንደነበር ገልፀዋል፡፡
“አገልግሎቱ በይበልጥ እየታወቀ እና የተጠቃሚ ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ አቅሙን እያሳደገ መምጣት ይኖርበታል” የሚሉት እኚህ ግለሰብ ማህበረሰቡን ለምሬትና ለእንግልት የሚዳርጉ ተግባራትን ማክሰም ወቅቱን የሚመጥን ተግባር እንደሚያደርገውም መስክረዋል፡፡
አቶ አብርሃም ተሾመ፤ በቅርንጫፍ ማዕከሉ የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን የደንበኞች አገልግሎት ሰጪ ባለሙያ ናቸው። ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በማዕከሉ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል፦ ቦሎ ማደስ፣ መንጃ ፍቃድ እግድ ማንሳት እና የመሳሰሉ እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡ ስለ አገልግሎት አሰጣጡ ሲያብራሩም፤ “አንድ አገልግሎት በዛ ቢባል እስከ አምስት ደቂቃ ይፈጃል፡፡ ተገልጋዮች ጉዳያቸውን በቶሎ ጨርሰን ስናሰናብታቸው ደስታቸው ከፍተኛ ነው። የማዕከሉ አገልግሎት ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ቆጣቢ ነው፡፡ አንድን አገልግሎት ለማግኘት መጥቶ እግረ መንገድ ሌሎች ጉዳዮቹን አንድ ቦታ ላይ መፈፀም ያስችላል” ብለዋል፡፡
የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ፣ ዘመናዊ እና የተሳለጠ አገልግሎት በመስጠት አዲስ አበባን ስማርት ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የሚናገሩት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ቦሌ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግስት፣ “የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት (ታህሳስ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ) ድረስ ቁጥራቸው ወደ 14 ሺህ 500 የሚሆኑ ባለጉዳዮችን ለማስተናገድ ችሏል፡፡ ተደራሽነታችንን የበለጠ ለማስፋት ለማህበረሰቡ ምን ምን አገልግሎት እንደምንሰጥ በማህበራዊ ሚድያዎቻችን የማሳወቅ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አገልግሎት ላይ ያሉ ውስንነቶችን ለማስቀረት ይቻል ዘንድ ያሉ አማራጮችን መተግበር ላይ ትኩረቱን ያደረገው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በማንኛውም ክፍለ ከተማ ላይ የሚገኝ ነዋሪ በዚህ ማዕከል ላይ አስፈላጊውን መረጃ ይዞ በመምጣት መገልገል የሚችልበት እድል አለ፡፡ ከሰኞ እስከ አርብ ከጠዋት 2፡30 እስከ ምሽት 1፡30 ሰዓት፣ ቅዳሜ እስከ 10፡30 ሰዓት እንዲሁም ምሳ ሰዓት ላይ የሚዘጋ አገልግሎት አለመኖሩን ጭምር አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዩ በነፃነት የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርግ የዘመነ የአሰራር ስርዓት ነው የሚሉት ደግሞ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ናቸው፡፡ በ2018 በጀት ዓመት በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች እንደሚከፈቱ ገልፀዋል፡፡
እንደ ሀገር የዘመነ የመንግስት አገልግሎትን ለመገንባት ያስችል ዘንድ ጠንካራና አዲስ የስራ ባህል መከተል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን መሰሉ ትልቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ለማስፈፀም ያስችል ዘንድ እንደ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ለዚህም ብቁ ባለሙያዎችን በማደራጀት ረገድ ቁጥራቸው 1 መቶ 51 ሰራተኞች የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ ለሌሎች አርዓያ መሆን እንዲችሉ እውቅና እንደተሰጣቸው ጭምር ገልፀዋል፡፡
አዲስ የሆነ የአገልግሎት አድማስ ለተገልጋዮች በማበርከት ረገድ ትልቅ ሚና ያለው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በእናት መስሪያ ቤቶች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች ዘመናዊ አሰራርን ተላብሰው እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት አድማሱን በማስፋት በቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ ተጨማሪ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱን ከፍቷል፡፡ የነዋሪውን የአገልግሎት ጥራትና ፍላጎት ከፍ ባለ ደረጃ እየከወነ የሚገኘው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት ግንባታቸው በተጀመረባቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ለሚ ኩራ እና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ላይ የተጀመሩ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ በአጭር ወራት ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፤ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ ተቋማትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በተለይ ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ የሆነውን የመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ደግሞ የመዲናዋን ነዋሪ ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡ በተለይም ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ስራዎችን የሚያስቀር መላ በመሆኑ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ ወደ እነዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመምጣት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጋብዘዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን