የአገልጋይነት ክህሎትን የሚያሳድገው ስልጠና

You are currently viewing የአገልጋይነት ክህሎትን የሚያሳድገው ስልጠና

ኢትዮ ኮደርስ የተሰኘው የ5 ሚሊዮን ሰልጣኞች ስልጠና እ.ኤ.አ እስከ 2026 በርካቶችን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የተዘጋጀ መርሃ ግብር ነው

በአዲስ አበባ ደረጃ በአጠቃላይ  892  ሺህ 51 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰጠ ባለው ስልጠና እስከ አሁን ድረስ 622 ሺህ 348 ማድረስ ተችሏል

የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ከሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መካከል ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ተጠቃሽ ነው። ይህ ስልጠና ለሁሉም ሰው አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይ  ደግሞ የመንግስት ሰራተኞች መሰልጠናቸው አገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል በማድረግ ረገድ የራሱ አይተኬ ሚና አለው፡፡

ስልጠናውን ከወሰዱ ሰራተኞች ውስጥ ወይዘሮ ቅድስት ክፍሌ አንዷ ናቸው፡፡ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኢኮኖሚ ዘርፍ ክፍል የንግድ አገልግሎት ቡድን የንግድ  ምዝገባና ፈቃድ ባለሙያ ናቸው፡፡ ወደ አዲስ መሶብ ከመምጣታቸው በፊት በንግድ ቢሮ  ለአምስት ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ አሁን በሚሰሩበት ተቋም አገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻልና ተገልጋዮችንም ለማርካት ዘመኑ የዋጀውን የኮደርስ ስልጠና ሰልጥነዋል፡፡

አራቱንም የስልጠና ፓኬጆች (መሰረታዊ ኘሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እንዲሁም አንድሮይድ ኘሮግራሚንግ) ስልጠናዎች ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀዋል፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቁ ያደረጋቸውም የዓመት ፈቃድ ወስደው ቤታቸው ሆነው መከታተላቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡

“ይህ የአጭር ጊዜ ስልጠና ተመቻችቶ መሰልጠን መቻሌ ስራዬን በቅልጥፍና እንድሰራ አድርጎኛል፡፡ ከዚህ በፊት በሲስተም እና ሌሎች ምክንያቶች ተገልጋዮች አገልግሎት እንዳያገኙ የሚያደርጉ ችግሮችን ለመፍታት እድል የፈጠረም ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለተገልጋዩም ጊዜንና እንግልትን ይቀንሳል” ይላሉ፡፡ 

እንደ ወይዘሮ ቅድስት ገለፃ፤ በቴክኖሎጂ ራሳቸውን ብቁ ማድረጋቸው አገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት የሚከተሉ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ለዚህም  ከዚህ በፊት አገልግሎት እየተሰጠ ባለበት ወቅት የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ባለሙያ እስኪመጣ የሚወስደውን ጊዜ ራሳቸው መፍታት የሚችሉበትን እውቀት በማግኘታቸው የኮደርስ ስልጠናው ጠቅሟቸዋል፡፡ “ስልጠናው አዳዲስ ልምምዶችን ወደ ህይወታችን ባስገባን ቁጥር የበለጠ ሌሎች ነገሮችንም ለማወቅ እንድንበረታታ ያግዘናል” ሲሉም አክለዋል፡፡ 

“ይህ ስልጠና የጊዜ አጠቃቀምን፣ ለራስ ህይወት እንዲሁም ለንባብ  እንዴት ከፋፍለን መጠቀም እንዳለብን አስተምሮናል” የሚሉት ወይዘሮ ቅድስት፤ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረጉት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

“ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ባለበት በዚህ ዘመን ይህን ስልጠና መውሰዴ ወደፊት አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር ከዚህ በተሻለ መንገድ ለመስራት እንድዘጋጅ የሚያደርግና ራሴን በቴክኖሎጂ እንዳበቃ የሚያበረታታ ነው፡፡ እውቀት ኖሮኝም ደስ ብሎኝ ስለምሰራ ውጤታማ እንድሆን ያደርገኛል” ይላሉ፡፡ 

“የኮደርስ ስልጠና መውሰዴ የቴክኖሎጂ እውቀቴ እንዲጨምርና ቀልጣፋ አገልግሎት እንድሰጥ አድርጎኛል” የሚሉን ደግሞ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የቤቶች ልማት አስተዳደር ባለሙያ አቶ ቃሉ አቤ ናቸው። ከዚህ ቀደም በከተማዋ ያሉ ሪል ስቴቶች እየተገነቡ ያሉና ግንባታቸው የተጠናቀቁ በማለት የመመዝገብ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ይህን ስራ ለማሻሻልና የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን ለማዳበር በሚል  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የኮደርስ ስልጠና ሲጀመር ከስራቸው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን ዳታ ሳይንስ  እንደወሰዱ ገልፀዋል፡፡

“ይህ ኮርስ ከመረጃ አያያዝ ብሎም ስራዬ ጋር ቀጥታ ስለሚገናኝ ቀድሜ ወስጃለሁ፡፡ ከዚያም በኋላ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከገባሁ በኋላ ቀሪዎቹን ሶስት ኮርሶች ሰልጥኜ  ማጠናቀቅ ችያለሁ፡፡ ስልጠናውንም በምሰራበት ኮምፒዩተር ሰዓቴን እያመቻቸሁ ነው የወሰድኩት፡፡ ይህን ስልጠና መውሰዴም መረጃዎችን እንዴት በቀላሉ ማደራጀት እንደምችል አስተምሮኛል፡፡ የነበረኝን የኤክስ ኤል እውቀት ወደተሻለ አሳድጎልኛል፡፡ አዲስ እይታንም ፈጥሮልኛል” ሲሉ ያገኙትን ጥቅም ዘርዝረዋል፡፡

የተገልጋይ እርካታ በእኛ የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታ ይመሰረታል የሚሉት አቶ ቃሉ፤ “በአሁኑ ወቅት ከተገልጋይ አያያዝ ጀምሮ መረጃዎችን በቀላሉ ማደራጀት ስላስቻለኝ ስራዬን  በቅልጥፍና እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ በአዲስ መሶብ ካለው አዲስ ቴክኖሎጂ ጋር ለመላመድ እንግዳ እንዳልሆንም አግዞኛል” በማለት ይናገራሉ፡፡

ስለ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ምንም እውቀት እንዳልነበራቸው ገልፀው፤  ከስልጠናው በኋላ ግን በዕለት ተዕለት ህይወታቸውም ላይ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ያነሳሉ፡፡ በአጠቃላይ የኮደርስ ስልጠና ከቴክኖሎጂ ጋር ያለንን ትስስር የሚጨምር በመሆኑ ሌሎችም ስልጠናውን ያልወሰዱ አካላት ሰልጥነው የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ ከራሳቸው ተሞክሮ ተነስተው ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ 

ሌላኛው በተቋሙ የዲጂታላይዜሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሊራንሶ ተሾመ፣ አዲስ መሶብ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የኮደርስ ስልጠናው መሰጠቱ ደግሞ የሰራተኞቹን የዲጂታል ክህሎት የሚያሳድግ ነው፡፡ ስራዎችን በአግባቡ እንዲሰሩ፣ የነበረባቸውን ክፍተት እንዲቀርፉ በእጅጉ ያግዛል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግም የተቋሙ 151 የሚሆኑ ሰራተኞች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

ለምሳሌ ያህልም “የዳታ አናላይሲስ ኮርስ” የመጣውን ተገልጋይ፣ የተቆረጠውን ትኬት ብዛት እንዲሁም ማን ብዙ ተገልጋዮችን እንዳስተናገደ የሚሰራ (የሚያደራጅ) ነው፡፡ ይህ አገልግሎት አሰጣጡን ለመቆጣጠርም ሆነ ሰራተኞች የመረጃ አያያዝ ክህሎታቸውን በማሳደግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ነው፡፡

ስልጠናው በስራ አካባቢ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል፡፡ ሀገር የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ መስመር ለማስያዝ ያግዛል፡፡ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ይጨምራል ሲሉ በቴክኖሎጂ የተካነ ዜጋ ለማፍራት ያለውን አጋዥነት አብራርተዋል፡፡

“የምጠቀምባቸው ነገሮች ሁሉ ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ቴክኖሎጂን አለማወቁ ስራዎችን ለመስራት ያስቸግራል” የሚሉት አቶ ሊራንሶ፤ ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሰው ስልጠናውን በመውሰድ የቴክኖሎጂ እውቀቱን ማሳደግ እንዳለበት ነው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አዋሌ መሃመድ፤ የኮደርስ ስልጠና ለሰራተኞች መሰጠቱ አገልግሎት አሰጣጡን የተቀላጠፈ ከማድረግ አንፃር ስላለው ፋይዳ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ ከተማችን በማያቋርጥ ፈጣን ለውጥ ላይ ናት፡፡ ለዚህም በቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት ተገቢ ነው፡፡ በቴክኖሎጂው ዘርፍም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ መንግስት ዜጎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንዲያተርፉ ለማስቻል ኢትዮ ኮደርስ የተሰኘው የ5 ሚሊዮን ሰልጣኞች ስልጠና እ.ኤ.አ እስከ 2026 በርካቶችን የዲጂታል ክህሎት እንዲኖራቸው ለማስቻል የተዘጋጀ መርሃ ግብር ነው፡፡ ከእነዚህ መካከል በስራ ገበታቸው ላይ ያሉ ሰራተኞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መካከል የተደረገ ስምምነት ሲሆን በዋናነት በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን፣ የስማርት ሲቲ ምሰሶ የሆነውን  ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ማህበረሰብ “ስማርት ፒፕል” ለመፍጠር፣ አዳዲስ የስራ እድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ሀገራችንን በቴክኖሎጂ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም ለፈጠራ ምቹ ሁኔታን ለማመቻቸት የሚረዳ ነው፡፡ 

በአዲስ አበባ ደረጃ በአጠቃላይ  892  ሺህ 51 ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ያለው ስልጠናው ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ግዜ ድረስ ከ622 ሺህ 348 በላይ ማድረስ ተችሏል፡፡ እቅዳችንን ያላሳካንበት ምክንያትም ብዙ ሰዎች ቢመዘገቡም ጊዜና ትኩረት ሰጥተው መከታተል ላይ ክፍተት በማሳያታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

ሰራተኛው ሃይል ወጣቱ የሰው ሃይል ነው ያሉት አቶ አዋሌ፤ ይህንን ሃይል በቴክኖሎጂው ላይ ውጤት እንዲያመጣ አብዛኛው በከተማዋ የሚከናወነው አገልግሎት ወደ ኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት  የመቀየር ስራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ በዚህም አጠቃላይ ካሉት 576 አገልግሎቶች ወስጥ 348 አገልግሎቶች በኦን ላይን እየሰጠን እንገኛለን፡፡  

ይህም ከግማሽ በላይ አገልግሎቱ ተደራሽ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ ያህልም በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 107 አገልግሎት እየተሰጡ ሲሆን በዚያ ማዕከል የሚሰሩ ሁሉም ሰራተኞች ኮደርስ ሰልጥነዋል፡፡ ይህም ማለት አገልግሎቱን ሲሰጡ እውቀቱ ኖሯቸው እንዲሰሩ ያስችላቸዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓታቸውን የተሻለና የተቀላጠፈ ለማድረግና ተገልጋዩ ማህበረሰብም በአጭር ጊዜ ተስተናግዶ ወደ ቤቱ እንዲመለስ  የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡ 

የኮደርስ ስልጠና የተሰጠውና የሚሰጠው ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን ስራ ለሌላቸው ወጣት የማህበረሰብ ክፍልም ነው ያሉት አቶ አዋሌ፤ እነዚህ ዜጎች ሰልጥነው በግላቸውም ይሁን በመንግስት ወደ ስራ መግባታቸው በስራቸው ውጤታማና አምራች እንዲሆኑ እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር መስተጋብር በመፍጠር ሶፍት ዌሮችን እያለሙ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል፡፡

የኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስጨበጥን ያለመ ሲሆን፤ ይህን እውን ለማድረግ እኛም በ2018  በጀት ዓመት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መቶ በመቶ መጠናቀቅ አለበት ባሉት መልዕክት መሰረት አጠቃላይ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማህበረሰቡ መንግስት ያመቻቸውን እድል ተጠቅሞ የኮደርስ ስልጠናውን በመሰልጠን ራሱን በቴክኖሎጂ ማሳደግ መቻል አለበት ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review