በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ከእነዚህ መካከል በልብ ወለድ እና በነባራዊ ገጸ-ባህሪያት መስተጋብር የሚተረክ “የኢትዮጵያ የስንዴ ሽግግር” (Ethiopia’s Wheat Transformation) የተሰኘ ፈጠራ የታከለበት ዘጋቢ ፊልም ተመርቋል። ፊልሙ በሎስ አንጀለስ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በግብርና ራስን የመቻል አስደናቂ ጉዞዋን ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ ተገልጿል።
ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች መቅረባቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የመጽሐፍ ምርቃት፣ የንባብ ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይና የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
የመጀመሪያዋ ሴት የረጅም ልብ ወለድ ደራሲ ፀሐይ መልአኩ “ዘባሲል” መጽሐፍ ይመረቃል። ደራሲዋ፣ መጽሐፉ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደምና አጥንት ተከፍሎባት የተረከባትን ታላቅ ሀገር ባለአደራ ሆኖ ለቀጣዩ ትውልድ እንዴት ማስተላለፍ እንዳለበት ይጠቁማል ብላለች። ፀሐይ መልአኩ ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ ካሳተመቻቸው መጽሐፍት መካከል፤ ቋሳ፣ አንጉዝ፣ ቢስራሄል፣ እመምኔት፣ የስሜት ትኩሳት 1 እና 2፣ የንሰሃ ሸንጎ፣ የጴጥሮስ ዋዜማ፣ ጀግና እንደ ቴዎድሮስ፣ ቆራጥ እንደ ጴጥሮስ፣ ግለታሪክ እና የተባ ትሩፋት ተጠቃሽ ናቸው። “ዘባሲል” መጽሐፍ በ399 ገፆች የተዘጋጀ ታሪክ ለበስ ልብ ወለድ ሲሆን ዛሬ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) ከቀኑ 8:00 ሰዓት ይመረቃል፡፡
በሌላ መረጃ በዛሬው ዕለት በደራሲ ሌሊሳ ግርማ በተጻፈው “በታችም በምድር” በተሰኘው ረጅም ልብ ወለድ መጽሐፍ ሂሳዊ ውይይት ይደረጋል፡፡ አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው፣ ደራሲ ቤተማርያም ተሾመ እና ደራሲ ምግባር ሲራጅ በመጽሐፉ ላይ የመወያያ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡ የመጽሐፉ ውይይት የሚደረገው 4 ኪሎ ኢክላስ ሕንፃ ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ ሲሆን ሰዓቱ ደግሞ ዛሬ ከ8:00 ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡
የስዕል አውደ ርዕይ
“የራስ መንገድ” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ በዮሴፍ ሰቦቅሳ (ሰናይት) የቀረበው ይህ የስዕል አውደ ርዕይ ታህሳስ 1 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተከፈተ ሲሆን እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ መስቀል አደባባይ አጠገብ በሚገኘው ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ባለው በፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ እየታየ ይገኛል፡፡
ፊልም
ለዓመታት በተመረጡ ሲኒማ ቤቶችና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲታይ የነበረው “ከርቤ” ፊልም አሁን ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንዲመለከቱት ተለቀቀ፡፡ አርቲስት ሄኖክ ወንድሙን ጨምሮ ከ50 በላይ ታዋቂና አዳዲስ ተዋንያን የተሳተፉበት ከርቤ ፊልምን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደወጣበት የፊልሙ ባለቤቶች በምርቃቱ ወቅት ገልጸው ነበር፡፡ ፊልሙ በትናንትናው ዕለት በናሆም መልቲ ሚዲያ አማካኝነት በዩቱብ ለእይታ በቅቷል፡፡
የቴአትር መርሃግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቅዳሜ ቀን 8፡30 ሰዓት ላይ 12ቱ እንግዶች እንዲሁም 11፡30 ሰዓት ባሎችና ሚስቶች ለእይታ ይበቃሉ፡፡ እሁድ በ8፡30 ሰዓት ንጉሥ አርማህ እንዲሁም በ11፡30 ሰዓት እምዬ ብረቷ፣ ማክሰኞች 11፡30 ሰዓት ሶስቱ አይጦች፣ ረቡዕ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ፣ ሐሙስ በ11፡30 ሰዓት ሸምጋይ እንዲሁም አርብ በተመሳሳይ ሰዓት ዴጊያ የተሰኙ ቴአትሮች በቴአትር ቤቱ ለእይታ ይቀርባሉ፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ደግሞ እሁድ በአሉ ግርማ (ቤርሙዳ) ለተመልካች ይቀርባል፡፡
በተያያዘ መረጃ “የመጨረሻው ፍርድ” አዲስ ቴአትር ባሳለፍነው ሐሙስ ተመርቋል፡፡ ጀርመናዊው ፀሐፊ በርቶልት ብሬሽት “The Final Judgment” በሚል ርዕስ የፃፈው ቴአትር “የመጨረሻው ፍርድ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተመርቋል፡፡ በማንያዘዋል እንደሻው እና በዶክተር ላውራ ኦሊቬ የተዘጋጀው ቴአትሩ በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅትና በጀርመን የባህል ተቋም (ጎተ ኢንስቲትዩት) ትብብር ፕሮዲውስ የተደረገ መሆኑንም ኤቨንት አዲስ ዘግቧል፡፡
በጊዜው አማረ