የአፍሪካ ዋንጫ ትውስታዎች

You are currently viewing የአፍሪካ ዋንጫ ትውስታዎች

የአፍሪካ ዋንጫ (AFCON) ከ60 ዓመታት በላይ የአፍሪካን የእግር ኳስ ትዕይንት ሲያደምቅ የኖረ ታላቅ ውድድር ነው። የዚህ ውድድር መወለድ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF) ከተመሰረተበት ጊዜ ጋር የተቆራኘ ነው። ካፍ የተመሰረተው በ1957 በሱዳን መዲና በካርቱም ሲሆን መስራች ሀገራቱ ደግሞ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ነበሩ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት ሀገራት አንድ ብለው የጀመሩት የአፍሪካ ዋንጫ ሲሰናዳ ስታዲየሞች በቀለማትና በአፍሪካውያን ልዩ ልዩ ዝማሬዎች ይደምቃሉ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ደጋፊዎች ያላቸው ስሜትና ከፍተኛ ድጋፍ ለውድድሩ ልዩ ድባብ ይፈጥርለታል። ግብጽ ደግሞ ውድድሩን ለሰባት ጊዜ በማሸነፍ በመድረኩ የደመቀች ሀገር ናት። 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ደግሞ ነገ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ መካሄድ ይጀምራል፡፡

እ.ኤ.አ በ2006 ግብጽ አዘጋጅ ሀገር ሆና ዋንጫውን ካስቀረች በኋላ በ34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ ኮትዲቯር ናይጄሪያን ሁለት ለአንድ አሸንፋ ዋንጫውን ከፍ በማድረግ ታሪኩን ተጋርታለች፡፡ ዘጠኝ ሀገራት ከዚህ በፊት የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅተው ዋንጫውን አስቀርተዋል። ግብፅ ሶስት ጊዜ የውድድሩ አዘጋጅ ሆና ዋንጫውን ስታነሳ፣ ጋና ሁለት ጊዜ በሀገሯ እና ደጋፊዋ ፊት ባለድል ሆናለች። ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ አልጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዝያ እና አይቮሪ ኮስት እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ራሳቸው በአዘጋጁት ውድድር ሻምፒዮና ሆነዋል። ግብጽ 26 ጊዜ በውድድሩ ላይ በመሳተፍ ክብረወሰን የያዘችበት ሲሆን፣ ኮትዲቯር በ25 እንዲሁም ጋና በ24 ሁለተኛ እና ሦስተኛ ላይ ስለመቀመጣቸው የካፍ መረጃ ያሳያል።

የአፍሪካ ዋንጫ ከምስረታው 1957 (እ.ኤ.አ) አንስቶ በርካታ ክብረ ወሰኖች የተመዘገቡበት  መድረክ ነው። የፈረንጆቹ 2023 የኮትዲቯሩ መድረክ ድረስም የተቀመጡ እና ሊሰበሩ የሚችሉ ክብረ ወሰኖችን አስመልክቷል፡፡ በ2023ቱ የኮትዲቯር አፍሪካ ዋንጫ የተመዘገቡ 119 ግቦች ብዛት በአፍሪካ ዋንጫ ብዙ ግቦች የተቆጠሩበት ክብረ ወሰን ሆኖ ተቀምጧል።

ግብፅ ይህንን መድረክ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን እ.ኤ.አ ከ1994 እስከ 2025 ድረስ 17 ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የቻለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ ቱኒዝያ በብዙ መድረኮች በተከታታይ በመሳተፍ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት፡፡ ፈርኦኖቹ ለመጨረሻ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ ያደረጉት በፈረንጆቹ 2010 ነበር፡፡ ግብጻዊው አሠልጣኝ ሀሰን ሼሀታ ለተከታታይ 3 ጊዜ ከግብጽ ጋር የአፍሪካ ዋንጫውን በማንሳት የሚስተካከለው አሠልጣኝ የለም፡፡ እነዚህ ክብረ ወሰኖች ግብፅ እጅግ ስኬታማ በነበረችባቸው ዓመታት የተመዘገቡ ስለመሆናቸው የአፍሪካ ኒውስ ዘጋባ ያሳያል፡፡

በአንድ የፍጻሜ ጨዋታ አንድ ብሔራዊ ቡድን ሲያሸንፍ ሁሉንም የማሸነፊያ ግቦች አንድ ተጫዋች በማስቆጠር ደግሞ የመጀመሪያውን እና በሱዳን አስተናጋጅነት የተካሄደውን መድረክ ማንሳት ግድ ይላል፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያን አራት ለባዶ አሸንፋ ዋንጫውን ስታነሳ አራቱም ግቦች የተቆጠሩት በሙሐመድ ዲያብ አል አታር ነበር፡፡ በቅርቡ የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆኖ በድጋሚ የተመረጠው ሳሙኤል ኤቶ ስድስት መድረኮች ላይ በመካፈል በአጠቃላይ 18 ግቦችን በማስቆጠር በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡ ሳላህ 10፣ ሳዲዮ ማኔ 8 ግቦችን ይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው መንግሥቱ ወርቁ 10 ግቦችን በማስቆጠር 8ኛ ላይ ይገኛል፡፡

በአንድ ጨዋታ ብዙ ግቦችን በማስቆጠር የኮትዲቯሩ ላውረንት ፓኩ ክብረ ወሰኑን የያዘ ሲሆን፣ ይህን ያደረገው ደግሞ ሱዳን ባስተናገደችው መድረክ ኢትዮጵያን 6 ለ 1 ሲረቱ ነበር። 5ቱ ግቦች የተቆጠሩት በላውረንት ፓኩ ነው፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ዋንጫ በብዙ የግብ ልዩነት የተጠናቀቁ ሦስት ጨዋታዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ በኮትዲቯር የተመዘገቡ ናቸው። ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በፈረንጆቹ 2008 የጋናን ብሔራዊ ቡድን 5 ለ 0 የረቱበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ንዳዬ ማሉምባ በአንድ ውድድር ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛውን የግብ መጠን በማስመዝገብ ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡ ተጫዋቹ በ2019 ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ በ1974 የአሁኗ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የቀድሞ ዛየር ዋንጫውን ስታነሳ ነው ይህን ማድረግ የቻለው፡፡ የጋናው አንድሬ አይው፤ የግብጹ አህመድ ሀሰን፣ የቱኒዝያው ዩሴፍ ሳካኒ እና የካሜሮኑ ሪጎበርት ሶንግ በስምንት የአፍሪካ ዋንጫ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ቀዳሚ ናቸው፡፡

ባለፉት ሦስት የአፍሪካ ዋንጫ መድረኮች በእያንዳንዳቸው 100 እና ከዚያ በላይ ግቦች ተቆጥረዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ክብረ ወሰኖችን ይዞ 2025 ላይ የደረሰው የአፍሪካ ዋንጫ ነገ ሞሮኮ ከኮሞሮስ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀምራል፡፡ ነገ በሚጀምረው የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫም አዳዲስ ቁጥራዊ መረጃዎች ሊመዘገቡ እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው፡፡

በተከታታይ 18 ጨዋታዎችን በማሸነፍ የዓለም ክብረ ወሰንን የያዘችው ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ እንግዶቿን ተቀብላለች። በሰኔ 2024 ዛምቢያን 2 ለ 1 በመርታት የጀመረችውን የድል መንገድ ባለፈው ወር በወዳጅነት ጨዋታ ዛምቢያን 4 ለ 0 እስከረታችበት ድረስ ቀጥሏል። በእነዚህ ጊዜያት በተጋጣሚዎቿ ላይ 55 ግቦች ስታስቆጥር፤ አራት ግቦች ብቻ ተቆጥረውባታል።

በአስራ አምስት ጨዋታዎች ደግሞ ግብ አልተቆጠረባትም። በኳታር 2022 የዓለም ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ በማለፍ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ የሆነችው ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫን ካነሳች 60 ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በኳታር የዓለም ዋንጫ አስደናቂ አቋም ያሳየችው እና የውድድሩ ክስተት የነበረችው ሞሮኮ የዘንድሮውን ዋንጫ ሊያነሱ ይችላሉ ከተባሉ ሀገራት መካከል አንዷ ናት ይላል የዘጋርዲያን ዘገባ።

በርካቶች ካሜሩን ባዘጋጀችው 33ተኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ውድድር ላይ ዋንጫ ያነሳችው ሴኔጋል በድጋሚ ታነሳለች የሚል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። አልጄሪያ ምንም እንኳን ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ደካማ አቋማ ብታሳይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ ቡድን የገነባች ትመስላለች። ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳችው ግብፅ፣ ካሜሩን፣ ናይጄሪያ እና ጋናም እንደዚሁ የአሸናፊነት ግምት ካገኙ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይገኙበታል፡፡

በሞሮኮ አዘጋጅነት የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከታህሳስ 12 እስከ ጥር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። በእግር ኳስ መሠረተ ልማቶቿ እና በብሔራዊ ቡድን ግንባታ ልቃ የምትገኘው ሞሮኮ በስድስት ከተሞች በተዘጋጁ ዘጠኝ ስታዲየሞች ነው ግዙፉን ውድድር የምታስተናግደው።

ውድድሩ ሲጀመርም እንደ ማራካሽ፤ ካዛብላንካ እና ራባትን ጨምሮ ታንጂር፣ አጋዲር እና ፌዝ ከተሞች ላይ ጨዋታዎቹ ይከናወናሉ፡፡ በምድብ አንድ ሞሮኮ ከኮሞሮስ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ፍልሚያው እንደሚጀምርም ይጠበቃል። በአፍሪካ ዋንጫ የሚካፈሉት ሁሉም ቡድኖች ከዚህ ቀደም ተሳትፎ ያላቸው ሲሆኑ፣ ቦትስዋና እና ኮሞሮስ ለሁለተኛ ጊዜ በመካፈል ዝቅተኛ የተሳትፎ መጠን ያላቸው ሀገራት ናቸው።

የአፍሪካ ዋንጫ የጨዋታ ሜዳ ከመሆኑ ባሻገር የአፍሪካን የፖለቲካ እና የማህበራዊ ገፅታ የሚያሳይ ነበር። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ሲያገኙ፣ ዋንጫው የአዲስ ማንነት እና አዲስ የብሔራዊ ኩራት ምልክት ሆኖ አገልግሏል። የአፍሪካ ዋንጫ ከጥቂት ሀገራት ውድድር ተነስቶ ወደ 24 ቡድኖች ተሳታፊነት ከደረሰ በኋላ የዓለማችን ትልቁ የአህጉር አቀፍ ውድድሮች አንዱ ሆኗል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review