የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን እያዘመነ ነው

You are currently viewing የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የታክስ አሰባሰብ ስርዓቱን እያዘመነ ነው

AMN – ታኅሣሥ 11/2018 ዓ.ም

“ዲጂታል ኢትዮጵያን” ዕውን ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን ተከትሎ፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በተለይም በገቢዎች ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ብልሽቶችንና ማጭበርበሮችን በማስቀረት ረገድ ሚናው የጎላ ሆኗል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት የመረጃ ቋቶችን ማስተሳሰሩ፣ ግብር ከፋዮች ቀደም ሲል የነበረባቸውን የቢሮክራሲ እንግልት እንዲቀንሱና ተቋሙም ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ አስችሎታል።

ቀደም ሲል የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN) ለመስጠት እያንዳንዱ ግብር ከፋይ በአካል ተገኝቶ ፎቶና አሻራ መስጠት ይገደድ እንደነበር ያስታወሱት፣ በአራዳ ቅርንጫፍ አነስተኛ ግብር ከፋዮች የደንበኞች አገልግሎት ቡድን መሪ ገነት አዋሎ፣ አሁን ግን በፋይዳ መረጃ ቋት አማካኝነት ሂደቱ እጅግ ቀላል መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ቡድን መሪዋ ገለጻ፣ የፋይዳ መረጃ በቀጥታ ወደ ገቢዎች የመረጃ ቋት ስለሚገባ ያለ ምንም መደራረብና ማጭበርበር የታክስ መለያ ቁጥር መስጠት ተችሏል።

ሌላዋ የገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ አገልግሎት ኦፊሰር ቤዛዊት በበኩሏ፣ ዲጂታል መታወቂያው ስራን ከማቅለሉም በላይ ደንበኞች ረጅም ሰዓት ሳይጠብቁ በዲጂታል ቁጥራቸው ብቻ አገልግሎት እንዲያገኙ መንገድ መክፈቱን አብራርታለች።

በገቢዎች ቢሮ አገልግሎት ሲያገኙ ያነጋገርናቸው ደንበኞችም በአዲሱ አሰራር መደሰታቸውን ገልጸዋል። ተገልጋይ አብዱ ሽኩር፣ ቀደም ሲል ለታክስ ጉዳይ የግድ በአካል መገኘትና አሻራ መስጠት ይጠበቅብን ነበር፤ አሁን ግን በዲጂታል መታወቂያው አማካኝነት በውክልናም ቢሆን ጉዳዮችን መጨረስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብሏል።

ሌላው ተገልጋይ አቶ ኢሳያስ በበኩሉ፣ የፋይዳ መታወቂያን መጠቀም ጊዜንና ጉልበትን ከመቆጠቡ ባለፈ መረጃዎች በቀላሉ እንዲገኙ በማድረጉ ማንኛውም ዜጋ መታወቂያውን ሊይዝ እንደሚገባ መክሯል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተቋማትን እርስ በእርስ በማስተሳሰርና ግልጽነት ያለው አሰራር በመፍጠር፣ የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ እያፋጠነው እንደሚገኝ ኤ ኤም ኤን በቅኝቱ ማረጋገጥ ችሏል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review