የግልና የቡድን የተዛባ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት በከተማዋ ሠላምና ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን እንደማይታገስ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አሳሰበ

You are currently viewing የግልና የቡድን የተዛባ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት በከተማዋ ሠላምና ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን እንደማይታገስ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አሳሰበ

AMN ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓ/ም

የግልና የቡድን የተዛባ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት በከተማችን ሠላምና ደህንነት ላይ የሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራትን እንደማይታገስ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አሳሰበ፤ አጠቃላይ የከተማው የጸጥታ ሁኔታ ተገምግሞ ለፀጥታ አካላቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ከምን ጊዜውም በላይ ሠላሟ የተጠበቀና የበርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችን ቀልብ እየሳበች ትገኛለች፤ ለከተማዋ መዘመንና ሠላማዊ መሆን በየደረጃው የሚገኘው የፀጥታ ኃይል 24/7 በትጋት መላውን ነዋሪ በማስተባበር በከተማችን ሠላምና ደህንነት እንዲኖር አስችሏል፡፡

የፀረ ሠላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመግታት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሮችን በመከላከልና አዘዋዋሪዎቹንም በህግ እንዲጠየቁ አድርጓል፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ በህፃናትና ታዳጊዎች እገታና ስርቆት ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጭምር ካሉበት በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

ከህብረተሰቡ ባህልና ሞራል ተቃራኒ የሆኑ መልዕክቶችን በማህበራዊ ሚዲያ ሲያሰራጩ የነበሩ ግለሰቦችን እንዲሁም የወንጀል መንስኤ የሆኑ ሺሻና አደንዛዥ ዕፆችን ሲያስጠቅሙ በነበሩ የንግድ ቤቶች ላይ ህጋዊ ርምጃ በመውሰድ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

ጥምር የፀጥታ ኃይሉ እነዚህ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በመገምገም ለፀጥታ አካላቱ አመራሮች ጥብቅ የስራ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፈንታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በመሩት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ ተቀብለው ሀገርን ለማፍረስ፣ የህዝቦችን ሠላም እና ደህንነት ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በማክሰም የሀገሪቱን ብሎም የመዲናዋን ሠላም ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በግምገማው የተዛባ ፖለቲካዊ እሳቤን ለማሳካት እና የግል ፍላጎትን ለማሟላት ኃይማኖትን እና ብሔርን ሽፍን በማድረግ ወረቀት የመበተን አዝማሚያ፣ አገልግሎት እንዲሰጡ በተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ላይ ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ ማድረግ፣ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ንግድ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራም ይገኛል፡፡

ቀጣይ በከተማችን የሚከናወኑ ህዝብ በአደባባይ ወጥቶ የሚያከብራቸው ህዝባዊና ኃይማኖታዊ ክብረ በዓላት፣ እንዲሁም አለም አቀፍ ኮንፈረንሶችና ፕሮግራሞችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሠላምን ለማደፍረስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከወዲሁ ሊቀጩ እንደሚገባም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ኃይማኖትን እና ማንነትን ሽፍን በማድረግ ህዝብ እንዳይረጋጋና እየተሰራ ያለውን ገበያ የማረጋጋት ስራ ለማጨናገፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ህዝቡን በማሳተፍ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን በቀጣይ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትና ዓለም አቀፍ መድረኮች ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር እንዳያጋጥም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራና የተቀናጀ የጸጥታ ስራ ይሠራል ያለው የፀጥታ ኃይሉ የህዝቦችን ሠላምና አንድነት ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ጸረ ሠላም ኃይሎችም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

ህብረተሰቡ በተለይም የመኖሪያ ቤት በሚያከራይበት ወቅት የተከራዮችን ማንነት መለየትና ማረጋገጥ እንዳለበት ሆኖ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙትም ካለበት ቦታ በመሆን በእጅ ስልኩ የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp እንዲሁም በፖሊስ የመረጃ ስልኮች 991፣ 0111-110111 በመጠቀም ማንኛውንም መረጃ እንዲሰጥ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ ጥሪ አቅርቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review