በ17ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር የሊጉ መሪ አርሰናል ከኤቨርተን የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል።
ምሽት 5 ሰዓት በሂል ዲክንሰን ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ አርሰናል መሪነቱን ለማስጠበቅ ሦስት ነጥቡ ያስፈልገዋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ ተደላድሎ ይመራው የነበረው የሊግ ደረጃ አሁን ላይ ልዩነቱ ሁለት ነጥብ ብቻ ሆኗል።
አርሰናል ባሳለፍነው ሳምንት ወልቭስን 2ለ1 ሲረታ ተቸግሮ ታይቷል።
የወልቭስ ወደ ግብ ክልሉ ተጠግቶ መከላከል ፈታኝ የሆነበት የሚካኤል አርቴታው ቡድን በዛሬው ጨዋታ ከኤቨርተን ተመሳሳይ አቀራረብ ሊገጥመው ይችላል።
መድፈኞቹ ባለፈው ዓመት የዋንጫ ህልማቸውን ካቀጨጩ ክለቦች መካከል አንዱ ኤቨርተን ነው።
የመርሲሳይዱ ክለብ ባለፈው ዓመት አርሰናልን በገጠመባቸው ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
ኤቨርተን በዛሬው ጨዋታ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ፈታኝ ይሆንበታል።
በተለይ የሴኔጋላዊያኑ ኢድሪሳ ጋና ጌ እና ኢሊማን እንጃዬ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማቅናት ትልቅ እጦት እንደሚሆን ተገምቷል።
በሸዋንግዛው ግርማ