የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ሙያተኞችን አስመረቀ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ ሙያተኞችን አስመረቀ

AMN ታኅሣሥ 11/ 2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጄንሲ ለ3ኛ ጊዜ የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ 2 ሺ 483 ሙያተኞችን አስመርቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ኤጀንሲው ባለፉት ሦስት ዓመታት በቴክኖሎጅ ፣ በሰውኃይል ፣ በአሰራር አደረጃጀት እንዲሁም ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር ላይ ትኩረት በማድረግ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና አመራርና ሰራተኛው ከቴክኖሎጅ ጋር ያለውን ቅርበት እና ትስስር በማጎልበት ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት ሚናው የጎላ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ስራ አስኪያጅ ተፈራ ሞላ አዲስ አበባ በእድገት ጎዳና ላይ መሆኗን አስታውሰው ይህንኑ የሚመጥን የሰው ሀይል ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ዘመኑን የዋጀ እና ወቅቱን የሚመለከት የሀገራችንን ብልፅግና የሚያረጋግጥ ሕዝብን ለማገልገል ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂ አገልግሎት ማሳለጫ ነው ያሉት አቶ ተፈራ ኤጀንሲው ከነበሩበት ችግሮች በመላቀቅ እና ሪፎርም በማድረግ የተሞክሮ መቅሰሚያ ማዕከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ፈጠራን ታሳቢ ያደረገ አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት ፣ ማመንጨት እና ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ስልጠናውን የወሰዱ የኤጀንሲው ሙያተኞች ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ለማህበረሰቡ ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በሦስት ዙር ከወረዳ እስከ ማዕከል ለሚገኙ አመራሮች እና ባለሙያዎች ስልጠና እንዲወስዱ መደረጉን በመድረኩ ተመላክቷል።

በመሀመድኑር ዓሊ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review