ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ በሚያደርጉ የስራ ዕድሎች ላይ ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ እንደሚገኝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ገለጹ
ኃላፊው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በመንግስት የድጋፍ ማዕቀፍ ዙሪያ ባዘጋጀው የወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ ነው ይህን የተናገሩት።
አዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ የልማት ሂደት ላይ ትገኛለች ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ እነዚህ ልማቶች ከሚፈጥሯቸው የስራ ዕድሎች ውስጥ ወጣቱን በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የስራ ዕድል ማዕቀፎችን መንግስት ስለማመቻቸቱ ተናግረዋል።
በእነዚህ የስራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን ታዲያ ወጣቱ ሙሉ ዝግጁነት ሊኖረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተለይም የሚፈጠሩ የስራ ዕድሎችን ሳይመርጡ የመስራት ባህልን ሊያዳብሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በከተማዋ ለሚገኙ 79 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ናቸው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ በዕቅድ ከተያዘው አንጻር የ83 በመቶ አፈጻጸም መኖሩን ተናግረዋል።
ከስራ ፈጠራው ጎን ለጎን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መመቻቸቱንም አቶ በላይ ደጀን በመድረኩ አንስተዋል።
በላይሁን ፍስሃ