የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገፅታ በአጭር ግዜ መቀየር እንደሚቻል ማሳያ መሆኑ ተገለፀ።
142 ከተሞችን በዓባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ከተሞች የምክክር መድረክ፣ የከተሞች የኮሪደር ልማትን አስመልክቶ የከተሞች የትብብር መድረክን በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በመክፈቻ መርሐ-ግብሩም የኢትዮጵያ የከተሞች ትብብር ዳይሬክተር አቶ አንዷለም ጤናው፣ በከተሞች እየተስፋፋ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ለማጠናከር የልምድ ልውውጥ መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ የከተሞችን ገፅታ በአጭር ጊዜ መቀየር እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ከድር አደም በበኩላቸው፣ በአዲስ አበባ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት መሠረተ ልማትን ከማሟላት እና የዜጎችን ኑሮ ምቹ ከማድረግ ባሻገር 24/7 የስራ ባህልን በማሳደግ ረገድ ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚሠሩ የልማት ስራዎች ለሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የስራ መለኪያ መሆን እንደሚችልም አመላክተዋል።
ከ120 በላይ ከተሞች በተሳተፉበት የከተሞች የትብብር መድረክ፣ በተለያዩ ከተሞች የተከናወኑ የልማት ስራዎች እና እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ የልምድ ልውውጥ እያካሄዱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ አባል ከተማ ከንቲባዎች በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የወንዝ ዳርቻ የኮሪደርና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በወንድማገኝ አበበ