ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ብሔራዊ ስትራቴጂ ግቦቹን እንዲመታ የኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢንተርኔት ትስስር መሠረታዊ አስቻይ ጉዳዮች መሆናቸውን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለዲጂታል ሽግግር ስኬት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እንደ “ቴክኖሎጂ ምግብ” እንደሚቆጠር ጠቁመዋል።
ማንኛውም የቴክኖሎጂ መሣሪያ ያለ ኃይል ሊሠራ እንደማይችል የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሁሉም አማራጮች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ማስፋት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ከተሞች የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ግን ይህንን ትስስር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም እነዚህን መሠረተ ልማቶች በማሟላት ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር እንደሚቻል በጽኑ አምኖ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል