አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ምቹና ተስማሚ እየሆነች ትገኛለች።
ከዚህ ቀደም የከተማዋ ጎዳናዎች ለእግረኛም ሆነ ለተሽከርካሪ ምቹ ባለመሆናቸው፣ እግረኛውና ተሽከርካሪው እኩል የሚጋፉባቸውና ለአደጋ የተጋለጡ ነበሩ።
በተለይም በየመንደሩ የሚኖሩ ታዳጊዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት አማራጭ ቦታ በማጣታቸው፣ ኳስ ለመጫወት የተሽከርካሪ መንገዶችን ለመጠቀም ይገደዱ ነበር። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ታሪክ ሆኖ አልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ለታዳጊዎች፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት ምቹ የሆነች ከተማን ለመገንባት በወሰነው መሠረት ዘመን ተሻጋሪ የልማት ሥራዎችን አከናውኗል።
በዚህም የከተማዋ ጎዳናዎች ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተስማሚ በሆነ መልኩ እንዲገነቡ ተደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ ውብ ጎዳናዎች የራሳቸው የሆነ የእግረኛና የሳይክል መስመር ተሰርቶላቸው፣ በአረንጓዴ ልማትና በአበቦች አጊጠው ለእግር ጉዞ እና ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እጅግ ምቹ ሆነዋል።
በእነዚህ የታደሱና አዳዲስ ጎዳናዎች ላይ ወጣቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና ጎልማሶች በነፃነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከት አሁን ላይ የተለመደ የከተማዋ ባህል ሆኗል።
ምቹ፣ ንፁህ፣ ጤናማና ለሁሉ ተስማሚ ከተማ!